ለቃጠሎ ቀርቦ የነበረው አስክሬን ነፍስ ዘራ
የ25 አመቱ ህንዳዊ ወጣት በሀኪሞች መሞቱ ተረጋግጦ አስክሬኑ ለመቀጣል ተራ እየጠበቀ በነበረበት ወደ ህይወት ተመልሷል
አጋጣሚውን ተከትሎ 3 ሀኪሞች ከስራ የታገዱ ሲሆን ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል
ሞቱ የታወጀው ህንዳዊ ወጣት በ11ኛው ሰዐት ወደ ህይወት መመለስ መነጋገርያ ሆኗል፡፡
ሀኪሞች አስፈላጊውን የአስክሬን ምርመራ አድርገናል ብለው መሞቱን ያረጋገጡለት የ25 አመቱ ሮሂታሽ ኩማር የተባለ ህንዳዊ ወጣት አስከሬኑ ከመቃጠሉ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከሸለብታው ነቅቷል፡፡
የመናገር እና የመስማት የጤና እክል ያለበት ኩማር ባሳለፍነው ሀሙስ የህመሙ ሁኔታ በድንገት በመክፋቱ ወደ ሆስፒታል ይወሰዳል፡፡
የህንድ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት በሚጥል በሽታ የሚሰቃየው ወጣት ወደ ሆስፒታል በደረሰበት ወቅት ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ ነበር፡፡
እንደ መገናኛ ብዙሀኑ ዘገባ ከሆነ ታድያ የኩማር ሰውነት መንቀጥቀጡን ሲያቆም ሀኪሞቹ ተገቢውን ምንም አይነት የአስከሬን ምርመራ ሳይደርጉለት በፍጥነት መሞቱን የሚገልጽ ሪፖርት አዘጋጅተውለታል፡፡
ቀጥሎም አስከሬኑ በህንድ ባህል መሰረት ወደ አስከሬን ማቃጠያ ስፍራ ይዛወራል አስገራሚው ነገር የተፈጠረውም እዚህ ላይ ነው፡፡
እሳቱ ከመቀጣጠሉ በፊት በቦታው የተገኙት ሰዎች ከወጣቱ አካል ላይ ያልተጠበቀ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ወደ አስክሬኑ ተጠግተው የተጠቀለለበትን ጨርቅ ሲከፍቱ እስትፋንስ እንዳለው ማረጋገጣቸውን ተከትሎ ወዲያው ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም በማግስቱ ህይወቱ አልፏል፡፡
አጋጣሚውን ተከትሎ የሆስፒታሉ ባለስልጣና ሦስት ሀኪሞችን ከሥራ አግደው አግደዋል፤ በተጨማሪም ፖሊስ በከፈተው ምርመራ አስከፊ ሁኔታን ሊያስከትል የነበረውን ቸልተኝነት እያጣራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ እና ሌሎች የህንድ ሚዲያዎች ጉዳዩን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡
ሚድያዎቹ አጋጣሚው በሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን የህክምና ቸልተኝነት አደገኛነት አመላካች ነው በሚል ቁጥጥርን ማጠናከር እና እንደዚህ አይነት ክስተቶች እንዳይደገሙ አስፈላጊው የህክምና ሂደቶችን መከተል እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡