አብዛኞቹ የዩክሬን ወታደሮች ግዛት አሳልፈው በመስጠት ከሩሲያ ጋር መደራደር እንደሚፈልጉ ተገለጸ
ከሀገሪቱ ጦር ሁለት ሶስተኛ ወታደሮች ጦርነቱን በአፋጣኝ ሊያስቆሙ የሚችሉ የትኛውንም አማራጮች መጠቀም እንደሚገባ ያምናሉ ተብሏል
ጦርነቱ ከተጀመረበት 2022 አንስቶ 100 ሺህ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች ከድተዋል
አብዛኛው የዩክሬን ወታደሮች ሩስያ አሁን በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ሁኔታ መደራደርን እንደሚመርጡ አዲስ ሪፖርት አመላከተ፡፡
የዩክሬን ወታደሮች የውግያ ሞራላቸው እየቀነሰ በሚገኝበት እና የሩስያ ሃይሎች ግስጋሴ እየጨመረ ባለበት ወቅት ወታደሮች የግዛት አሳልፎ በመስጠት መስማማትን እና የተኩስ አቁም አማራጮችን እያስቀደሙ እንደሚገኙ ዘ ኢኮኖሚስት የዩክሬን ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዘገባው የወጣው የሩስያ ጦር በዶንባስ ክልል ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ወደፊት እየገፋ እንደሚገኝ እየተነገረ በሚገኝበት ጊዜ ነው፡፡
እየከፋ የመጣውን የዩክሬን የሰው ሀይል እጥረት ተከትሎ ሀገሪቱ አዳዲስ አባላትን በግዳጅ ለመመልመል የምታደርገው ጥረት የፍላጎቷን ያህል እንዳልሆነ ተሰምቷል፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት በአሁኑ ወቅት በግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ጦሩን እየተቀላቀሉ የሚገኙት ዜጎች እድሚያቸው እስከ 45 የሚጠጋ የውግያ ተነሳሽነት እና ሞራል የሌላቸው ናቸው ብሏል፡፡
የዩክሬን መገናኛ ብዙሀን የጦርነቱን አንድ ሺህ ቀናት መድፈን አስመልክቶ ባወጡት መረጃ ከ2022 ጀምሮ 100 ሺህ የሚጠጉ ዩክሬናውያን ከጦሩ መክዳታቸውን ወይም መጥፋታቸውን ዘግበዋል፡፡
በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች እየተባባሰ የመጣውን የሰው ሀይል ሁኔታ አስመልክቶ ጥቂት ወታደሮች እስከመጨረሻው ድረስ ለመዋጋት ፈቃደኛ ሲሆኑ በርከት የሚሉት ደግሞ አሁን ባለው የግዛት ሁኔታ ከሩሲያ ጋር ተደራድሮ ጦርነቱ እንዲቆም እንደሚፈልጉ ተሰምቷል፡፡
በዚህም መሰረት ዘ ኢኮኖሚስ አሰባሰብኩት ባለው ድምጽ ሁለት ሶስተኛ የሰራዊቱ አባላት የሀገራቸውን ግዛት አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው፡፡
ለሰላም ድርድር ክፍት እንደሆነች የምትናገረው ሞስኮ በበኩሏ ድርድሮች “በመሬት ላይ ያለውን እውነታ” ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው አሳስባለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዶኔስክ፣ ሉሀንስክ፣ ኬርሶን እና ዛፖሮዚያ ግዛቶችን እንዲሁም ክሬሚያን አሳልፈው የመስጠት እድል እንደማይኖራቸው በመግለጽ የሰላም ስምምነት በዩክሬን የግዛት ስምምነትን ማካተት አለበት ብለዋል።
የተጠቀሱት አምስቱም ክልሎች በተከታታይ ህዝበ ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ሩሲያን መቀላቀላቸው አይዘነጋም፡፡