“ስልጣን የኔ ነው የሚሉ አካላት ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም እየጣሩ ነው”- አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ይህን ያሉት በወቅታዊ የፀጥታ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ነው
አቶ ጌታቸው የትግራይ ፖለቲካ ወደ ከፋ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑን በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ "ስልጣን የኔ ነው የሚሉ አካላት" በፓርቲው ውስጥ የትግራይን ህዝብ ጥቅም ያላማከለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱን ማንነታቸውን በግልጽ ይፋ ያላደረጓቸው አካላት “በጉልበትም ቢሆን ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ግጭትና ትርምስ የሚፈጥሩ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ነው” በሚል ወቅሰዋል፡፡
- በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሰሰ
- በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት “አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት አንስቻለሁ” አለ
ፕሬዝዳንቱ ትኩረታችን በትግራይ ህዝብ ላይ መሆን ሲገባው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ቡድኖች ተወስዷል የሚሉትን ስልጣን መልሶ ለማግኘት አደገኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው በትግራይ ወቅታዊ ፣ የጸጥታ እና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ጉባኤ አከናውኛለሁ ያለው ሃይል የውሸት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቡን እያሳሳተ ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም “በትግራይ ሁሉንም ነገር ሲቆጣጠር የቆየው ሃይል አሁንም የጸጥታ ሃይሉን እና ሚዲያውን በመቆጣጠር እና በተለመደው መንገድ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ከጠላት ጋር እየተደራደረ ነው” ሲሉ ኮንነዋል፡፡
ጠላት በሚል የገለጻቸው አካላት የትኞቹ እንደሆኑ በግልጽ ባይናገሩም፤ “ይህ ቡድን ሰራዊቱ ከጎናችን ነው እያለ የጸጥታ ሃይሉን ለመከፋፈል እየሰራ ያለው ስራ የግለሰቦችን የስልጣን ጥማት ለማርካት ያለመ ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም የትግራይ ፖለቲካ ወደ ከፋ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑን በስጋትነት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ “በዞኖችና ወረዳዎች ስርዓት የሌለው ህገወጥ አሰራር እየተሰራ ነው” ብለዋል።
በሁለቱ ህውሓቶች በባለፈው አመት መጨረሻ አካባቢ በሰፊው ልዩነቶች ጎልተው መንጸባረቃቸውን ተከትሎ በደብረጽዮን ገብረሚካኤ (ዶ/ር) የሚመረው ቡድን በምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጠው ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከአባልነታቸው መነሳታቸውን እና ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ፓርቲውን ወክለው ክልሉን ማስተደደር እንደማይችሉም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይህን አስመልክቶ በትላንቱ መግለጫቸው ያብራሩት አቶ ጌታቸው የፖለቲካ ልዩነቱ አንገብጋቢ በሆኑ ትግራይን በሚመለከቱ ጉዳዮች እንዲሁም ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት መመለስ ላይ ሙሉ ትኩረት ሰጥተን እንዳንሰራ አድርጎናል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም “የምክር ቤት አባላትን በማነሳሳት የአስተዳዳሪዎችን ስልጣን መቀየር መፈንቅለ መንግስት ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው ፤ “መንግስትን የሚበተኑ መድረኮች በክልል በጀት እየተካሄዱ ነው” ብለዋል።
የፌዴራል መንግስት ችግራችሁን ፈትታችሁ አንድ የመሆን መንገድ መፍጠር አለባችሁ የሚል አቋም እንዳለውም በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል።
ልዩነቶች በዕርቅና በድርድር ለመፍታት እርሳቸውና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ ባልደረቦቻቸው ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።