የሊባኖሱ ታጣቂ ጥቃቱን የፈጸመው እስራኤል ቅዳሜ ዕለት ያለማስጠንቀቂያ በማዕከላዊ ቤይሩት የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው
የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ በትላንትናው ዕለት ብቻ 250 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፉ ተነገረ፡፡
ከጥቂት ወራት ወዲህ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ነው በተባለው የሮኬት ጥቃት እስካሁን 7 ሰዎች መቁሰላቸው ተሰምቷል፡፡
የተወሰኑ ሚሳኤሎች በዋና ከተማዋ ቴልአቪቭ አቅራቢያ ያረፉ ሲሆን በርካቶቹ በአየር መቃወሚያ መክሸፋቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል፡፡
ሄዝቦላህ የትላንቱን ጥቃት የፈጸመው እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በቤይሩት ላደረሰችው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ነው፡፡
የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ያለማስጠንቀቂያ በማዕከላዊ ቤይሩት ባደረሰው ጥቃት 29 ሰዎች ሲሞቱ 67ቱ ቆስለዋል።
እስራኤል የቅዳሜው ጥቃት የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው ደቡባዊ የከተማ ዳርቻ የሄዝቦላህ የማዘዣ ማዕከላት እና የስለላ ክፍሉ ኢላማ አድርጓል ብሏል።
በደቡብ ምዕራብ በታይሪ እና ናኩራ በተባሉ አካባቢዎች መካከል በአንድ ጦር ማዕከል ላይ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት አንድ የሊባኖስ ወታደር ሲገደል 18 ሰዎች መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጦር አስታውቋል፡፡
የእስራኤል ጦር ጥቃቱ የተፈፀመው ከሄዝቦላህ ጋር በሚደረግ ውጊያ ላይ እንደሆነ እና የወታደራዊ እርምጃው በታጣቂዎቹ ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆኑን በመግለጽ በሊባኖስ ወታደር ህልፈት ማዘኑን አሳውቋል፡፡
በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሊባኖስ ጦር በአብዛኛው ገለልተኛ ሆኖ ቢቆምም በተለያዩ ጥቃቶች ከ 40 በላይ የሊባኖስ ወታደሮች ተገድለዋል።
እስካሁን እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች በአጠቃላይ ከ3700 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጦርነቱ ወደ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከሊባኖስ አንድ አራተኛውን ህዝብ አፈናቅሏል።
በእስራኤል በኩል ወደ 90 ወታደሮች እና ወደ 50 ንጹሀን በሰሜን እስራኤል በቦምብ ጥቃት ተገድለዋል፤ ወደ 60,000 የሚጠጉት ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በቀጠናው የአሜሪካ ልዩ ልኡክ አሞስ ሆይስተን እስራኤል እና ሂዝቦላ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተጨማሪ ጫና እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሄዝቦላህ የተስማማበት የተኩስ አቁም ሀሳብ ከእስራኤል መንግስት ይሁንታን እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡