በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ከግመል ጋር ግንኙነት ያለው ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገለፀ
“የወረርሸኙን ምንነት እና መንስዔ ለመለየት እየሰራሁ ነው”- ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ወረርሹኙ እስካሁን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በ198 ሰዎች ላይ ተከስቷል- የዓለም ጤና ድርጅት
በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ከግመል ጋር ግንኙነት አለው የተባለ እና ለጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአል ዐይን አማርኛ እንዳስታወቀው፤ ወረርሽኙ በግመሎች ላይ መከሰቱን እና ከወርሽኙ ጋር በተያያዘ በሰዎች ላይም ምልክቶች ተከስተዋል።
በህብረተሰብ ኢንስቲትዩት የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር መስፍን ወሰን ለአል ዐይን እንደተናገሩት፤ “መንስኤው ያልታወቀ የግመሎች ሞት ነው የተከሰተው፤ የበሽታ ምልክት የታየባቸው ሰዎችም አሉ” ብለዋል።
የበሽታውን መንስኤ ለመለየት ከግብርና ሚኒስቴር እና በእንስሳት ጤና ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ስፍራው የባለሙያዎች ቡድን መሰማራቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የግመሎቹ ናሙና ተወስዶ ‘ናህሊክ’ ወደተባለ የእንስሳት ህክምና ላቦራቶሪ ተልኮ መንስኤው እየተጣራ መሆንኑም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ከሰዎች ላይ ናሙና በመውሰድ መንስኤው ምንድነው የሚለውን ለመለየት ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል።
“በሰዎች ላይ ከኢንፉሌንዛ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምልክት ተስተውሏል” ያሉት አቶ መስፍን፤ በሽታውም ሳዑዲ አረቢያ አካባቢ በብዛት የሚገኘው “ሜርሲኮቭ” የተባለ በሽታ ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ እንዳለም ተናግረዋል።
“ምልክቶቹ በሰዎች ላይ ተስተውሏል” ያለው ኢንስቲትዩት፤ ስንት ሰዎች ላይ ተከስቷል የሚለው ላይ “የላቦራቶሪ ምርመራ ካደረኩ በኋላ ነው ይፋ የማደርገው” ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ከግመል ጋር ግንኙነት ያለው ወረርሽኝ መከሰቱን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
እስከ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በደረሰው ሪፖርትም በኦሮሚያ ክልል 158 ሰዎች፤ በሶማሌ ክልል 40 ሰዎች ላይ በድምሩ 198 ሰዎች ላይ ወረርሽኙ መከሰቱን አስታውቋል።
ከእነዚህም ውስጥ 40 ሰዎች ለህክምና ሆስፒታል ገብተው የህክምና ክትትል ማድጋቸውን እና 35 ሰዎች ደግሞ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዝ እስካሁን የተመዘገበ ሞት የለም ብሏል።
ከፍተኛ ሆነ ትኩሳት፣ ተቅማጥ እና ማስመለስ የበሽታው ምልክቶች ናቸው ያለው ድርጅቱ፤ የበሽታውን መንስኤ ለመለየት የላቦራቶሪ ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው ብሏል።