ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የጀመረችው ጉዞ በኮሮና ወረርሽኝ እና በሌሎችም ምክንያቶች ተጓቷል ተባለ
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚስችላትን ሂደት በአውሮፓውኑ 2003 መጀመሯ ይታወሳል
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል “የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የሚደረገው ጉዞ በ2022 ይጠናቀቃል ብለን ነበር” ብለዋል
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን በአውሮፓውያኑ 2022 ለማጠናቀቅ ዕቅድ ይዛ እንደነበር የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዓለም የንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት በአውሮፓውያኑ 2022 ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር ገልጸው፤ የኮሮና ወረርሽኝ ግን ብዙዎቹን የጊዜ ሰሌዳዎች ማዛባቱን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ወረርሽኙ እስከመቸ ድረስ ተፅዕኖ እያደረሰ ሊቆይ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ሂደቱ መቀጠሉን ግን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚስችላትን ሂደት የጀመረችው በአውሮፓውኑ 2003 የነበረ ቢሆንም፤ 2010 በኋላ ግን የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጦ ሂደቱ ቶሎ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ መላኩ ያስታወቁት፡፡
“ከዓለም ተነጥለን የትም መድረስ አንችልም”ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ የተጀመረው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት በጥሩ ሂደት ላይ በመሆኑ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነትን ጉዳይ የማጠናቀቅ ስራዎች መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ አባል ለመሆን ካሉት ሂደቶች አንዱ የሆነውና አራተኛው ስብሰባ ተብሎ የሚጠራው መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ አምስተኛው ስብሰባም እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለሚቀርቡላት ጥያቄዎችን መልስ እየሰጠች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ መልስ የመስጠቱ ሂደት ሲጠናቀቅ ሌሎች ስራዎች የበለጠ ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ፤ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ስትሆን የማንም ሀገር ሸቀጥ ማራገፊያ ትሆናለች” በሚል የሚነሳው ሀሳብም ከግንዛቤ ጉድለት የመነጨ እንደሚመስላቸው አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ በአማካይ የኢትዮጵያ ታሪፍ 17 በመቶ አካባቢ እንደሆነና ይህንንም እስከ 52 በመቶ ወደላይ መለጠጥ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
አቶ መላኩ፤ ታሪፍን ከሁኔታዎች ጋር በማያያዘ እየቀነሱና እየጨመሩ መሄድ እንደሚቻል የገለጹ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል በመሆኗ ታሪፎችንና ከለላዎችን በሙሉ አንስታ፤ የዓለም ምርት እየገባ የሚራገፍበት ሁኔታ እንደሌለና ድርጅቱም በባህሪው እንደዛ እንዳልሆነ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅትና የአፍሪካ ነጸ የንግድ ቀጠና ስምምነቶች፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ መስራት ያለባትን የተሻለ እንድትሰራ የየራሳቸው ዕድል እንዳላቸው ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅት የሚመራው በስምምነት በመሆኑ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ የገለጹት አቶ መላኩ፤ ሁሉም ነገር የሚመሰረተው ግን ኢትዮጵያ በሚኖራት ጥንካሬ ልክ ነው ብለዋል፡፡
6 ሺ 372 የሚደርሱ የኢትዮጵያ ምርቶች እና በ5 ዘርፎች የተከፋፈሉ አገልግሎቶች፤ ተሰልተው ኢትዮጵያ ምን አላት፤ ከማን ላይ ምን ትፈልጋለች የሚሉት ጉዳዮች ታስቦባቸው እየተሰሩ መሆኑንም ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ ሰላሟ እስካስከበረችና ተወዳዳሪ እስከሆነች ድረስ በንግድ ስምምነቶች ተጠቃሚ እንጅ ተጎጅ እንደማትሆን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በአውሮፓውያን 2003 የጀመረችው ሂደት መቸ ይጠናቀቃል የሚለውን ትክክለኛ የጊዜ ሰሌዳ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን አቶ መላኩ አለበል ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አሁን ላይ ሌሎች ሀገሮች ለኢትዮጵያ፤ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ያሉ ሲሆን እነዚህ ጥያቄዎችና ኢትዮጵያ የምንሰጣቸውን ምላሾች መሰረት ተደርጎ ስለሚወሰን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡