የእንስሳቱ መጠለያ ጠባቂዎች የግለሰቡን ግማሽ የሰውነት አካል ከአንበሶቹ አስጥለዋል
ዕጮኛውን ለማስደሰት በሚል ወደ አንበሶች የቀረበው ሰው በእንስሳቱ ተበላ፡፡
የ44 ዓመቱ ኢሪስኩሎቭ የምስራቅ እስያዋ ኡዝቤኪስታን ዜግነት ያለው ሲሆን ፓርኬንት በተሰኘችው ከተማ ይኖር ነበር፡፡
በእንስሳት መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በጥበቃ ሙያ ያገለግል የነበረው ይህ ሰው እጮኛውን ለማስደሰት ሲል ለየት ያለ ነገር ለማድረግ ያቅዳል፡፡
ተቀጥሮ በሚሰራበት የእንስሳት መጠለያ ውስጥ ከአፍሪካ የመጡ ሶስት አንበሶች ያሉ ሲሆን ወደነዚህ እንስሳት ቀርቦ ለመቀረጽም ይወስናል፡፡
እንዳለውም ግለሰቡ አንበሶቹ ወደ ሚኖሩበት ስፍራ በማቅናት ሶስቱን አንበሶች በስማቸው እየጠራ እንዲወጡ በሩን ይከፍትላቸዋል፡፡
ከአንበሳ ጋር የሰልፊ ፎቶ ለመነሳት የሞከረ ግለሰብ በደረሰበት ንክሻ ሞተ
ይህ ሰውም ይህን ሁሉ ሲያደርግ ራሱን በተንቀሳቃሽ ስልኩ እየቀረጸ ነበር የተባለ ሲሆን አንበሶቹ በራቸው እንደተከፈተላቸው ወዲያውኑ ጥቃት ያደርሱበታል፡፡
በአንበሶቹ ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ይህ ሰውም ሰዎች እንዲረዱት ጩኸት ማሰማቱን ተከትሎ ሌሎች ጥበቃዎች ሊረዱት ሲመጡ አብዛኛው የሰውነት ክፍሉ በአንበሶቹ ተበልቶ እና ህይወቱ አልፎ ይደርሳሉ፡፡
ጥበቃዎቹ አንዱን አንበሳ ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ቀሪ የሰውነት ክፍሉን ማትረፍ እንደቻሉ የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ዘግይቶ በተደረገ ማጣራትም ግለሰቡ በራሱ ፈቃድ ፍቅረኛውን ለማስደሰት ወደ አንበሶቹ እንደቀረበ እና አንበሶቹ ጉዳት እንደማያደርሱበት ለማሳየት ያደረገው ጥረት እንደሆነ በስልኩ ላይ የተገኘው የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ ያስረዳል፡፡
ጥበቃዎቹም ቀሪ የሰውነት ክፍሉን ለቤተሰቦቹ እንዳስረከቡ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡