ከአንበሳ ጋር የሰልፊ ፎቶ ለመነሳት የሞከረ ግለሰብ በደረሰበት ንክሻ ሞተ
አንበሳው አሁን ላይ ወደ ኬጅ ውስጥ ገብቶ ክትትል እየተደረገበት ነው ተብሏል
ፕራሀልድ ጉጃር የተባለው ህንዳዊ ግለሰብ 12 ሜትር ከፍታ ያለውን የግቢ አጥር በመውጣት ለአንበሳው ወደተከለለ ቦታ ገብቷል
ከአንበሳ ጋር የሰልፊ ፎቶ ለመነሳት የሞከረ ግለሰብ በደረሰበት ንክሻ ሞተ።
በደቡባዊ ህንድ ለአንበሳው ወደተከለለ ቦታ ዘሎ በመግባት የሰልፊ ፎቶ ለመነሳት የሞከረው ህንዳዊ ግለሰብ በደረሰበት ንክሻ ህይወቱ ማለፉን የፎሪስት ዲፓርትመንት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ባለስልጣናቱ እንደገለጹት በአንድራ ፖራድሽ ግዛት ትሩፖቲ ውስጥ በሚገኘው የእንስሳት ፖርክ ፕራሀልድ ጉጃር የተባለው ግለሰብ 12 ሜትር ከፍታ ያለውን የግቢ አጥር በመውጣት ለአንበሳው ወደተከለለ ቦታ ገብቷል።
ዘ ኢንዲፔንደንት የአካባቢውን ሚዲያዎች ጠቅሶ እንደዘገበው ከራጃስታን ግዛት መምጣቱ የተገለጸው ጉጃር ወደ ግቢው በመግባት ከአንበሳ ጋር ሰልፊ ፎቶ ለመነሳት ሙከራ አድርጓል።
እንደዘገባው ከሆነ ጉጃር ይህን ያደረገው ሰክሮ ሊሆን ይችላል።
የትሩፖቲ ፖሊስ ማሊካ ጋርግ እንደገጸፈው የፖርኩ ጥበቃ ግለሰቡ አጥሩን እየወጣ በነበረበት ወቅት ሊያስቆመው ሞክሮ ነበር። ነገርግን ግለሰቡ ዘሎ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ላይ አርፏል።
ጉጃር ጥበቃው እየሮጠ ሲጠጋው ዘሎ ውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ላይ በማረፍ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት አንበሶች የከበበውን 12 ሜትር ከፍታ ያለውን አጥር መውጣቱን ፖሊስ ጋርግ ተናግሯል።
"ጉጃር አንበሶቹ ፊት ለፊት ዘሎ አረፈ። አንበሶቹም ነክሰው ገደሉት"
አንበሶቹ ተንከባካቢያቸው መጥቶ ወደሚመገቡበት ቦታ አባብሎ እስከሚያርቃቸው ድረስ እና አስከሬኑ እስከሚነሳ ድረስ፣ ከአስከሬኑ ፊት ቆመው ነበር።
ፖሊሶች የጉጃር ቤተሰቦችን ለማግኘት መሞከራቸውን እና የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለበት ለማረጋገጥ መሞከራቸውን ገልጸዋል። አንበሳው አሁን ላይ ወደ 'ኬጅ' ውስጥ ገብቶ ክትትል እየተደረገበት ነው ተብሏል።