ፍቅረኛዋን በጨለማ ለማግኘት ስትል የመንደሩን መብራት የምታጠፋው አፍቃሪ
እንስቷ ፍቅረኛ እንዳላት የመንደሩ ሰው እንዳያያት በሚል በየቀኑ ምሽት ላይ መብራት ስታጠፋ ቆይታለች
ምሽቱን በጨለማ ማሳለፍ የሰለቻቸው ነዋሪዎችም ለመብራት ሀይል ቢያመለክቱም ተቋሙ የተፈጠረ ብልሽት አለመኖሩን ገልጿል
በሕንድ ምዕራባዊ ክፍል ቢሀር ግዛት ከሰሞኑ ዓለም ጉድ ያሰኘ ድርጊት ተፈጽሟል።
በዚህ ግዛት ቤቲያህ የተሰኘ ማህበረሰብ አካል የሆነች እንስት በአቅራቢያዋ ባለ መንደር ውስጥ የሚኖር ጉብል ትወዳለች።
ከዚህ ጉብል ጋር ፍቅር የጀመረችው ይህች እንስት ፍቅሯን ማንም እንዲያቅባት አልፈለገችም።
ሰው እንዳያያቸው በሚልም የመንደሩን መብራት በማጥፋት ምሽት ላይ ፍቅረኛዋን እንደልቧ ስታገኝ ቆይታለች።
ሁሌ ምሽት በመጣ ቁጥር ጨለማ የሚውጣቸው የመንደሩ ነዋሪዎችም የመብራት ሀይል እንዲጠግንላቸው አቤቱታ ያቀርባሉ።
ከደንበኞቹ አቤቱታ የቀረበለት መብራት ሀይልም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቱ አስተማማኝ መሆኑን ምንም አይነት ብልሽት አለመኖሩን ይገልጻል።
ይሁንና አሁንም ምሽት ላይ እንደተለመደው የመብራት መጥፋቱ መቀጠል ያሳሰባቸው ነዋሪዎች ምሽቱን አድፍጠው ማን እንደሚያጠፋው ለመያዝ ይጠባበቃሉ።
ይህች አፍቃሪ እንደተለመደው ፍቅረኛዋን በጨለማ ለማግኘት ስትል መብራቱን ስታጠፋ እጅ ከፍንጅ ይዘዋታል።
አንስቷ ድርጊቱን ለምን እንዳደረገችው ለነዋሪዎቹ ብታስረዳም የተበሳጩ ነዋሪዎች ሊደበድቧት ሲሞክሩ ፍቅረኛዋ ደርሶ አስጥሏታል።
ፍቅረኛዋ የአካባቢውን ሰው ይዞ በመምጣት ከአደባባይ ድብደባ የዳነችው ይህች አፍቃሪ ምስል በመላ ሕንድ ተሰራጭቶ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
የአካባቢው ሽማግሌዎችም ይህች የፍቅር ሰው ፍቅሯ ለምን በጨለማ ብቻ ይወሰናል በሚል ከመከሩ በኋላ ፍቅረኛሞቹን ረድተው እንዲጋቡ አድርገዋል ሲል ኢንዲያን ቱዴይ ዘግቧል።