ለ2600 አመታት ሰምጦ የነበረው ጥንታዊ መርከብ ከውሀ ውስጥ ወጣ
በ7ኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ ምስራቅ ስፔን ውሃ ዳርቻ ሰምጦ የነበረው መርከብ ሙዚየም ውስጥ ገብቷል
መርከቡ በአሁኑ ሶሪያ ፣ ሊባኖስ እና እስራኤል አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ለንግድ ይጠቀሙበት የነበረ መሆኑ ታውቋል
የስፔን አርኪዮሎጂስቶች 2600 ዓመታት በውሀ ውስጥ ያስቆጠረውን መርከብ ከደቡባዊ ምስራቅ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ በተሳካ ሁኔታ ማውጣት ችለዋል።
በቅርስነት የተመዘገበው ይህ የመርከብ ስባሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በ1994 ነው ተብሏል፡፡
የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎቹ የመርከቡ ስባሪ ከተገኘ በኋላ አካባቢውን ከተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመገደብ መርከቡን ሳይበላሽ ወደ ምድር የሚያወጡበትን መንገድ ሲመራመሩ ቆይተዋል፡፡
የስፔን የባህል ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት መርከቡ በ7ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ እና በዚሁ ጊዜ ባጋጠመው አደጋ ስለመስመጡ ጠቅሟል፡፡
“ማዛሮን ሁለት” የሚል ስያሜ ያለው መርከብ ከባህር ውስጥ ከወጣ በኋላ በቅርቡ በስፔን ብሔራዊ የውሃ ውስጥ አርኪዮሎጂ ሙዚየም ለዕይታ እንደሚበቃ ታውቋል፡፡
14 ባለሙያዎች የተሳተፉበት ቡድን የመርከቡን ቅርጽ ሳይበላሽ ከውሀ ለማውጣት የተለያዩ የቅርስ መጠበቂያ ቴክኒኮችን ከተጠቀሙ በኋላ በሁለት ወራት ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መርከቡን ማውጣት ችለዋል፡፡
በምስራቃዊ ሜድትራኒያን በ7ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አብቦ የነበረው “የፎኔሽያ” ስልጣኔ ህዝቦች ንብረት እንደሆነ የተነገረለት መርከብ፤ በአሁኑ ጊዜ በሊባኖስ ፣ እስራኤል እና ሶሪያ ተብለው በሚጠሩ አካባዎች የሚገኙ ነጋዴዎች ይጠቀሙበት እንደነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡
ፎኔሽያውያን በንግድ እንቅስቃሴያቸው የበለፀጉ እና በጥንታዊቷ ግሪክ እና ሮም ለተዘጋጁት ፊደሎች መሠረት የሆነ ፊደል ስለመስራታቸው የሚነገር ሲሆን የዚህ የሥልጣኔ አሻራዎች ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት እንደጠፉ የታሪክ ምሁራኑ ያስረዳሉ፡፡
በቫሌንሲያ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ዲ ሁዋን ይህ ግኝት ከከፍተኛ ጥንታዊ የቅርስ አይነቶች የሚመደብ ስለመሆኑ ተናግረው በወቅቱ የነበረው ስልጣኔ ከየብስ ባለፈ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለመድረስ መርከቦችን ጥቅም ላይ መዋሉ የስልጣኔውን ደረጃ ያሳል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከአንድ ቦታ ወደ አንድቦታ ለመጓጓዝ መርከበኞች ይጠቀሙበት የነበረው የካርታ አይነት እንዲሁም የመርከቦቹ አሰራር እና ዲዛይን ለዘመናዊው አለም ትልቅ ትምህርት የሚያበረክት ግኝት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከውሀ ውስጥ የወጣውን የመርከብ ስባሪ ለረጅም አመታት ባህር ውስጥ እንደመቆየቱ ሳይበላሽ ለእይታ እንዲበቃ ጥገና እና ሌሎች እንክብካቤዎች እየተደረጉለት ይገኛል፡፡