የበሽር አላሳድ ደጋፊዎች በጸጥታ ሀይሎች ላይ በከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት 14 ሰዎች ተገደሉ
በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ 10 ሰዎች ተጎድተዋል
አዲሱ አስተዳደር በቀድሞው መንግስት ስር የተለያዩ ወንጀሎችን የፈጸሙ ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረቱን ቀጥሏል
ሶሪያ ምዕራባዊ ክፍል በበሽር አላሳድ መንግስት ደጋፊዎች በተፈጸመ ጥቃት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር 14 የጸጥታ ሀይሎች ተገደሉ፡፡
የጸጥታ ኃይሎቹ በዋና ከተማዋ ደማስቆ አቅራቢያ በሚገኘው በታዋቂው የሳይድናያ እስር ቤት ውስጥ ከነበረው ሚና ጋር በተያያዘ የቀድሞ የፖሊስ መኮንንን ለመያዝ ሲሞክሩ አድፍጦ በነበረ ሀይል ጥቃት ተከፍቶባቸዋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት በሜዲትራኒያን ባህር ታርቱስ ወደብ አቅራቢያ የአሳድ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአላዊት ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት አከባቢ በተካሄደው ውግያ ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች 10 ወታደሮች ቆስለዋል፡፡
ጥቃቱን ከፈጸሙት አካላት ሶስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የአማጺ ቡድኑ ተጨማሪ ወታደሮችን በመላክ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጥቃቱን ፈጽመው የሸሹ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአካባቢው ባለስልጣነት በታርቱስ እና ሆምስ ከተሞች ላይ የሰአት እላፊ ገደብ ጥለዋል፡፡
እነዚህ አካባቢዎች የአሳድ ቤተሰብን ጨምሮ የቀድሞ የአገዛዙ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች የሚኖሩባቸው ሲሆኑ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የፈጸሙ ባለስልጣናት አሁንም ተደብቀው እንደሚገኙባቸው በአዲሱ አስተዳደር ይታመናል፡፡
የቀድሞ ወታደራዊ መኮንኖች የጦር መሳሪያ ለማስረከብ እና እጅ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደሉም፤ በአንዳንድ ከተሞች ውስጥም ነዋሪዎችን በማስተባበር የመዋጋት ፍላጎት እንዳላቸው ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
አልዋቲ በመባል የሚታወቀው የሺአ እስልምና እምነት ሀይማኖታዊ መሪዎች በስፍራው የሚገኙ የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናት ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጥረት ቢያደረጉም አመራሮቹ ከጦር ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚፈለጉ በመሆኑ አልተሳካም፡፡
በሶሪያ እስር ቤት ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች አሁንም በዘመዶቻቸው ላይ ለደረሰው በደል እና ፍትህን እየጠበቁ ናቸው።
በዚህም ግድያ እና ማሰቃየትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀል የሚፈለጉ ባለስልጣናት ላይ የህግ ቅጣት እንዲተላለፍም በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኤችቲኤስ በተባለው የአማጺ ቡድን መሪነት መንግስት ለማዋቅር ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ጎንለጎን በአሳድ መንግስት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ የቀድሞ ባለስልጣናት እና አመራሮችን አድኖ ለመያዝ ስራዎች ቀጥለዋል፡፡