ፈረንሳይ ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማቀራረብ ሚስጥራዊ ውይይት ለማካሄድ ለሞስኮ ጥያቄ ማቅረቧን ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፓሪስ የዩክሬንን ጦር ለማጠናከር ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያደርጉ ምዕራባውያን መካከል አንዷ ነች ብለዋል

ሚኒስትሩ በአመታዊ ማጠቃላያ መግለጫቸው ላይ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ባሳዩት ፍላጎት የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲራመዱ እየጠበቅን ነው ብለዋል
ፈረንሳይ ዩክሬን በቀጥታ ባልተሳተፈችበት ሁኔታ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያግዙ ግንኙነቶችን ለመመስረት ሚስጥራዊ ስብሰባ ለማካሄድ ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርባ እንደነበር ተገለጸ፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በአመቱ ማጠቃለያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፓሪስ የውይይት ሙከራ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ከያዙት አቋም በተቃራኒ የተደረገ መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል፡፡
ለዚህ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም “ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሁለቱን ሀገራት ከማቀራረብ እና ለማወያየት ከመጣር ይልቅ የሞስኮን የደህንነት ስጋቶች ወደ ጎን በመተው ጦርነቱን መደገፍ ላይ አተኩረዋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “ሩሲያ መሰል ውይይቶችን ለማካሄድ ፈቃደኛ ብትሆንም፤ ፈረንሳይ ወደ ዩክሬን ሰላም አስከባሪ እንዲላክ ሀሳብ ያቀረበች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን ፣ የዩክሬን ወታደሮችን እያሰለጠነች እንደምትገኝ እና የሩሲያን ጦር መምታት የዩክሬንን የመደራደር አቅም እንደሚያጠናክረው ጽኑ እምነት እንዳላት አንዘነጋም” ብለዋል፡፡
አዲሱን የትራምፕ አስተዳደርን ጨምሮ አሁንም የሰላም አማራጮችን ለማስቀደም ከሚሰሩ የትኛውም ወገኖች ጋር ለመስራት ሞስኮ ዝግጁ መሆኗን ላቭሮቭ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ነገር ግን የዩክሬን ጦር እንደገና እንዲደራጅ ፣ ተጨማሪ ጦር መሳሪያዎችን ለማግኝት እና ለጊዜ መግዣ ሊውል የሚችል ፣ ወደ ሰላም የማይመራ ፣ ያልተጠና የተኩስ አቁም ስምምነትን አንቀበልም ብለዋል ሚኒስትሩ
ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጦርነት ማስቆም ጥረቶች ጋር ተያይዞ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ትራምፕ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲራመዱ እየጠበቅናቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትራምፕ የዩክሬን ልኡክ የሆኑት ኪት ኬሎግ ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ንግግሮች ዝግጁ መሆናቸውን ትራምፕም ጦርነቱን ማቆም የሚያስችል ስምምነትን ለመፈጸም ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ በቅርቡ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ተናግረው ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭም ከጦርነቱ በኋላ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የዘለቀው የሞስኮ እና የዋሽንግተን ግንኙነት በትራምፕ አስተዳደር እንደሚሻሻል እምነታቸው መሆኑን ገልጸው፤ ሆኖም ውጥረቱን የጀመረችው አሜሪካ እንደመሆኗ ግንኙነቱን ለመቀጠልም ቀዳሚ ሃላፊነት አለባት ብለዋል።