ከፈረንጆቹ ገና ማግስት አሜሪካ እና ብሪታንያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የሚከበረው “የቦክሲንግ ደይ” በዓል ምንድን ነው?
ከ1743 ጀምሮ መከበር የጀመረው በዓል ግብይቶችን በማድረግ ፣ ስጦታ በመቀያየር እና ስፖርታዊ ውድድሮችን በመመልከት ይከበራል
በዛሬው ዕለትም ማንችስተር ሲቲ ፣ ዩናይትድ ፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲን ጨምሮ 8 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ “የቦክሲንግ ደይ” ተጠባቂ ጨዋታዎችን ያከናውናሉ
ከፈረንጆቹ ገና ማግስት የሚከበረው በተልምዶ “ቦክሲንግ ደይ” በመባል የሚታወቀው በዓል እንግሊዞች እንዳስጀመሩት ይነገራል፡፡
የገና በዓልን ድባብ ለማራዘም ታስቦ መከበር እንደተጀመረ የሚነገርለት ሲሆን እንደ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም ፣ በኮመን ዌልዝ ሀገራት እና በደቡብ አፍሪካ ይከበራል፡፡
ቦክሲንግ ደይን የሚያከብሩ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከገና የተረፉ ምግቦችን በመገበያየት ፣ ግብይቶችን በመፈጸም፣ ስጦታ በመቀያር እና ስፖርታዊ ውድድሮችን በመመልከት ቀኑን ያሳልፉታል፡፡
በዕለቱ እግር ኳስ ክሪኬት ፣ ራግቢ ፣ የፈረስ ውድድር እና አደንን የመሳሰሉ የስፖርት አይነቶች በርካቶች የሚመለከቷቸው ውድድሮች ናቸው፡፡
“ቦክሲንግ ደይ” የሚለውን ስያም እንዴት እንዳገኝ ሁለት መላ ምቶች ተቀምጠዋል፤ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያናት በገና ቀን ያገኟቸውን የገንዘብ ልገሳዎች በማግስቱ ልብስ እና ገንዘብን ጨምሮ በሳጥን ውስጥ በማድረግ ለድሆች ከመስጠታቸው ጋር እንደሚገናኝ የሚነገር ነው፡፡
ሌላው ደግሞ ሀብታሞች እና ንጉሳውያን ቤተሰቦች ከገና በአል የተራረፏቸውን ምግቦች እና ጥቂት ስጦታዎችን በመጨመር በሳጥን ለአገልጋዮቻቸው ከሚሰጡት ስጦታ ጋር ስያሜው እንደሚያያዝ ያመላክታል፡፡
ይህንንም መነሻ በማድረግ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ኩባንያዎች በ”ቦክሲንግ ደይ” የቦነስ ክፍያን ጨምሮ የተለያዩ ስጦታዎችን ለሰራተኞቻቸው ይሰጣሉ፡፡
የበዓሉ መነሻ በሆነችው ብሪታንያ ከ1800 ጀምሮ ቀኑ ይፋዊ ክብረ በአል ሆኖ የሚከበር ሲሆን በአውስትራሊያ ፣ ካናዳ ፣ ኒውዝላንድ ፣ እና በሆንግ ኮንግ በይፋ ስራ ተዘግቶ ይከበራል፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ከ100 አመት በኋላ ቀኑን ይፋዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር አድርጋለች፡፡
አሜሪካ በሀገሪቱ ተወዳጅ የሆነውን የቅርጫት ኳስ ውድድር በገና ዕለት ታከናውናለች፡፡
በአንጻሩ በእንግሊዝ ማንችስተር ሲቲ ከኤቨርተን ፣ ቼልሲ ከፉልሀም ፣ ወልቭስ ከማንችስተር ዩናይትድ ፣ ሊቨርፑል ከሌስተር ሲቲ የሚያደርጉትን ግጥሚያ ጨምሮ 8 “የቦክሲንግ ደይ” ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ፡፡
በተጨማሪም በዛሬው እለት 11 የፈረስ ግልቢያ ውድድሮች እንዲሁም የራግቢ እና የክሪኬት ፍልሚያዎች የበዓሉ ታዳሚዎች በስፋት የሚመለከቷቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ናቸው፡፡