ጾታዊ ጥቃት ደርሶባት ለመክሰስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደችው ህንዳዊት በፖሊስ ተደፈረች
የታዳጊዋ የመደፈር ዜና በመላ ህንድ ትልቅ ቁጣ ቀስቅሷል ተብሏል
በህንድ በአማካኝ በየ18 ደቂቃው አንድ ሴት እንደምትደፈር ሪፖርቶች ያመለክታሉ
በሰሜን ህንድ በቡዱን ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞብኛል ብላ ለመክሰስ ፖሊስ ጣቢያ የሄደችው የ13 ዓመት ታዳጊ በፖሊስ መደፈሯ አነጋጋሪ ሆነዋል፡፡
አሁን ላይ ታዳጊዋን የደፈረ ፖሊስ ከስራው የተገደ ሲሆን ፤ በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ ለማቅረብ ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን የኡታር ፕራደሽ ግዛት ፖሊስ ጣቢያ ኃለፊ አስታውቋል፡፡
ታዳጊዋ ባለፈው ወር በአራት ወንዶች መደፈሯን ተናግራለች፡፡የታዳጊዋ የመደፈር ዜና በመላ ህንድ ትልቅ ቁጣ መቀስቀሱን በማህበራዊ ሚዲያ በመዘዋወር ያሉ አስተያየቶች አመልክተዋል፡፡
የታዳጊዋ ወላጅ ባቀረቡት ክስ፤ አራቱ ወንዶች ሴት ልጃቸውን የደፈሯት ለአራት ቀናት ያክል ማደያ ወደ ተባለ ግዛት ወስደው እቤት ውስጥ በመዝጋት ነበር ብሏል፡፡
አራቱም ወንዶች ለአራት ቀናት ከደፈሯት በኋላ ወደ መኖሪያ አከባቢዋ መልሰው ጥለዋት መሰወራቸውንም ነው ወላጅ አባቷ የገለጹት፡፡
አሳዛኙ ነገር ደግሞ ፤ በሚቀጠለው ቀን ታዳጊዋ ከአክስቷ ጋር በመሆን ክስ ለመመስረት ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደች ቢሆንም፤ በፖሊስ ጣቢያው ኃላፊ እንደተደፈረች ኤን-ዲቲ-ቪ የተባለ የህንድ ቻናል ዘግቧል፡፡
ዜናውን ተከትሎ በግዛቱ ያሉትን ህጎች ጥያቄ ውስጥ መግባታቸው በመነገር ላይ ያለው፡፡
የህንድ ኮንግረስ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሪያንካ ጋንዲ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ‘‘ፖሊስ ጣቢያዎች ለሴቶች ደህንነት አስተማማኝ ካልሆኑ ፤ ሴቶች ታዲያ የት ሄደው ይከሳሉ?’’የሚል ትችት አዘል መልእክት አጋርቷል፡፡
እንደፈረንጆቹ 2012 አንዲት ወጣት ሴት በደልሂ ከተማ በአውቶቡስ ውስጥ በወንዶች ተደፍራ ሞሞቷን ተከትሎ፤ ህንድና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ጉዳይ አነጋገሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዚህም ህንድ መሰል ወንጀል በሚፈጽሙ አካላት ላይ አዲስ ህግ ለማስውጣት እስከመገደድ የደረሰችበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል፡፡
እንደፈረንጆቹ 2020 በመሰል የወንጀል ተግባር ተሳትፈዋል ባለቻቸው አራት ሰዎች ላይ የሞት ፍረድ መበየኗም የሚታወስ ነው፡፡ይሁን እንጂ፤ የህንድ መንግስት ህግና የቅጣት እርምጃዎች ወንጀሉን ሊያስቆሙት እንዳልቻሉ ነው በመነገር ላይ ያለው፡፡
ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፤ በ2020 ብቻ በህንድ 28 ሺህ 317 ሰቶች ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡አሃዙ በአማካኝ በየ 18 ደቂቃው አንድ ህንዳዊት ሴት ትደፈራለች እንደማለት ነው፡፡