ልጄን ያለ እኔ እውቅና ቀብራችኋል ያለው ግለሰብ 14 ሰዎችን ተኩሶ ገደለ
ልጁ መሞቱን ያልሰማው ይህ ግለሰብ በሟች ልጁ ስርዓተ ቀብር ላይ የተገኙ ሰዎችን እንደገደለ ተገልጿል
ከሟቾቹ ውስጥ ዘጠኙ ህጻናት ናቸው ተብሏል
ልጄን ያለ እኔ እውቅና ቀብራችኋል ያለው ሰው 14 ሰዎችን ተኩሶ ገደለ።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኡጋንዳ ድንበር አዋሳኝ በሆነችው ድጆጎ ክልል ነዋሪ የሆነው ግለሰብ የዲሞክራዪክ ኮንጎ ባህር ጦር አባል ነው ተብሏል።
ይህ ወታደር በውትድርና ቦታው እያለ ልጁ በህመም ህይወቱ አልፏል የተባለ ሲሆን ቤተሰቦቹ እና የአካባቢው ሰው ህይወቱ ያለፈውን ህጻን ስርዓተ ቀብር ይፈጽማሉ።
ወታደሩ ሀገር አማን ብሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ልጁ ህይወቱ ማለፉን እና ስርዓተ ቀብሩም መፈጸሙ ይነገረዋል።
በሁኔታው ያዘነው ይህ ወታደር ያለእኔ እውቅና እንዴት ልጄን ትቀብራላችሁ በሚል ተኩስ መክፈቱን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ወታደሩ በተኮሰው ጥይት ዘጠኝ ህጻናትን ጨምሮ የ14 ሰዎች ህይወት አልፏል።
በነዋሪዎች ላይ ተኩስ የከፈተው ይህ ወታደርም በአካባቢው ወዳለ ጫካ ቢገባም ቆይቶ ግን ለህግ አስከባሪዎች እጅ መስጠቱ ተገልጿል።
የ32 ዓመት እድሜ አለው የተባለው ይህ ወታደር የህግ ሂደቱ በወታደራዊ ፍርድ ቤት በመታየት ላይ እንደሆነም ተገልጿል።
ፔፔ ንዶምቤ የተሰኘው ይህ ወታደር ዋና ማዘዣው ትቾሚያ በተሰኘው ስፍራ ያደረገ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ባህር ሀይል አባል ነውም ተብሏል።
ግድያው በተፈጸመበት አካባቢ ያለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በበኩሉ በጥቃቱ ቆስለው የነበሩ አዛውንት እንዲሁም በድንጋጤ በልብ ድካም ሁለት ሰዎችም ህይወት ማለፉን ገልጿል