የጃፓን ዓቃቤ በቀደሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ግድያ በጠረጠረው ግለሰብ ላይ ክስ መሰረተ
በሺዎች የሚቆጠሩ ጃፓናውያን በግድያ በተጠረጠረው ያማጋሚ ላይ የተመሰረተውን ክስ ተቃውመዋል
ሺንዞ አቤ ጃፓንን ለሁለት ያህል ጊዜያት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ናቸው
የጃፓን ዓቃቤ ህግ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በመግደል በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ ክስ መመስረቱን የጃፓኑ ዮሚዩሪ ጋዜጣ ዘግቧል።
የናራ ዲስትሪክት ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት የግድያ ክስ የመሰረተው በ42 ዓመቱ ጃፓናዊ ተጹያ ያማጋሚ ላይ ነው፡፡
ዓቃቤ ህግ ያማጋሚ ላይ የግድያ ወንጀል ክሱን የመሰረተው የጠመንጃ ህጎችን በመጣስ ለስድስት ወራት ያህል የአዕምሮ ህክምና ምርመራ ካጠናቀቀ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
ይሁን እንጅ ያማጋሚ በልጅነት እድሜው በእናቱ ዘንድ ችላ ተብሎ እንደማደጉ የአዕምሮ ችግር ሊኖርበት ይችላል የሚሉት ጃፓናውያን የህግ ስርዓቱ ታሳቢ የሚያደርጋቸው ነገሮች እንዲኖሩና በተከሳሹ ላይ ርህራሄ እንዲኖረው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ወደ 15 ሺህ የሚገመቱ ሰዎችም አቃብያነ ህጎች በያማጋሚ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ቀላል እንዲሆን የሚጠይቅ አቤቱታ ፈርመዋል ሲሉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በሃምሌ ወር ለፓርቲያቸው በመቀስቀስ ላይ ሳሉ በሰሜን ምዕራባዊ የሃገሪቱ ክፍል ናራ ከተማ ጎዳና ላይ ከአንድ ግለሰብ ሽጉጥ በተተኮሰ ጥይት የተገደሉበት አጋጣሚ ዓለምን ያስደነገጠ አሳዛኝ ክስተት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ግድያው ጥብቅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ ያላት ጃፓን ልል የባለስልጣናት ጥበቃ ስርዓት እንዳላት ያጋለጠና የጸጥታ መዋቅሩን ያስተቸ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
አቤ በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በፈቃዳቸው ስልጣን እስከለቀቁበት ወቅት ለሁለት ያህል ጊዜያት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡
ሺንዞ አቤ ስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲይዙ በዕድሜ ትንሹ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።
አቤኖሚክስ በሚል ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናቸው ሃገራቸውን ግዙፍ ምጣኔ ሃብትን ከገነቡ ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ ችለው የነበረም ሲሆን ጃፓን በተሻለ የዲፕሎማሲ እመርታ ላይ እንድትደርስ ስለማስቻላቸው በሰፊው ይነገራል።