95 በመቶ እንስሳት የሰው ድምጽ ሲሰሙ በፍርሃት በርግገው እንደሮጡ ተመራማሪዎች ተናገሩ
በደቡብ አፍሪካ የተደረገ ጥናት በዱር እንስሳት ላይ የሰዎች ድምጽ ከአንበሳ በበለጠ ፍራቻ እንደሚያስከትል ጠቁሟል።
ተመራማሪዎች በኩሩገር ብሄራዊ ፓርክ በተደበቀ የድምጽ ማጉያ ሰዎች መደበኛ ወሬ ሲያወሩ አሰምተዋል።
በዚህም 95 በመቶ እንስሳት ድምጹን ሲሰሙ እጅግ በጣም ፍርሃት እንዳደረባቸው እና በርግገው እንደሮጡ ተናግረዋል።
በአንጻሩ ደግሞ የሚጮህና የሚያጉረመርም የአንበሳ ድምጽ ሲሰሙ ያን ያህል ፍርሃት አልተነበበባቸውም ብለዋል።
በሙከራው ወቅት አንዳንድ ዝሆኖች የአንበሳውን ድምጽ ሲሰሙ ድምጹ ወደመጣበት አቅጣጫ በመዞር ለመጋፈጥ መሞከራቸው ተነግሯል።
የጥናቱ ውጤት ድኩላ፣ ነብር፣ ዝሆን፣ ቀጭኔና ከርከሮን የሚያካትቱት እንስሳት ከሰው ጋር መገናኘት አደገኛ መሆኑን እንደሚረዱ አመልክቷል።
ለዚህም አደን፣ የጦር መሳሪያን መጠቀምና እንስሳቱን ለመያዝ በውሻ ማሳደድ ምክንያት እንደሆነ ጥናቱ ጠቁሟል።
ጥናቱ በዱር ህይወት በአጠቃላይ እንስሳት ከሌሎች አሳዳጅ አውሬዎች ይልቅ ሰውን ይፈራሉ ብሏል።
ተመራማሪዎቹ ይህም በዱር ተሪዝም ላይ ጠባሳ ያሳድራል ብለዋል። ጎብኝዎች ለመጎብኘት የሚፈልጓቸው እንስሳት በፍርሃት እንደሚርቋቸው ተናግረዋል።