ባንኩ ለማገገም ከ45 ዓመታት በላይ ይወስድበታል ተብሏል
ለአፍሪካ ምጣኔ-ሀብት ስኬት አርአያ ተደርጋ የምትነሳው ጋና ታይቶ በማይታወቅ የፋይናንስ ቀውስ እየታመሰች ነው።
በዚህ ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በ2022 በጀት ዓመት 5.2 ቢሊዮን ዶላር በመጥፋቱ የማዕከላዊ ባንክ ገዢዎች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጠይቀዋል።
ሰልፉን ያስተባበረው ተቃዋሚው ናሽናል ዲሞክራቲክ ኮንግረስ ማዕከላዊ ባንክ ገንዘቡን አትሞ ለመንግስት ሰጥቷል ሲል ከሷል።
ይህም እርምጃ ጠንካራ አቅም የነበረው የሀገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ እንዲዳከምና የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ አድርጓል ብሏል።
ተቃዋሚው በውስጣዊ ኦዲት የተገኙ ውጤቶችን ይዞም መንግስት ባለፈው ዓመት ለአዲስ የቢሮ ግንባታዎች 250 ሚሊዮን ዶር ወጪ መደረጉን ተችቷል።
የባንኩን ገዢ በግዴለሽነትና በአስተዳደር እንዝላልነትም ከሷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምጣኔ-ሀብት ባለሞያዎች ቀውሱን ታይቶ የማይታወቅ ያሉት ሲሆን፤ ለማገገም ከ45 ዓመታት በላይ ይወስዳል ብለዋል።
ባንኩ የአስተዳደር ችግር የለብኝም ብሎ የካደ ሲሆን፤ ችግሩን ከፍ ዝቅ በሚለው የምንዛሬ ተመን እና የመንግስት ተቋማት ብድር ባለመክፈላቸው የመጣ ነው ሲል ጣቱን ወደ ሌላ ቀስሯል።
መንግስት 700 ሚሊዮን ዶላር ለመበደር መወሰኑ እና ብድሩን አለመክፈሉ ለቀውሱ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነውም ብሏል።