የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ስነ-ስርዓት በሚቀጥለው ሳምንት አርብ ይካሄዳል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እና የሩሲያ መንግስት ተቀናቃኝ አሌክሲ ኔቫሊን ከቀናት በኋላ የሚበረከተውን የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁት መሀል ናቸው።
ሆኖም ባለሞያዎች የሴቶች፣ የነባር ሰዎችና የአካባቢ ተሟጋቾች ሽልማቱን በእጃቸው ሊያስገቡ ይችላሉ ብለዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት የሚበረከተው የኖርዌይ ሽልማት፤ እንደከዚህ ቀደሙ አሸናፊው ከተጠበቀው ውጭ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ሆኖም ግን በግመታ የሚታወቁ ሰዎች የ2023ን የኖቤል የሰላም ሽልማት የዩክሬኑ ዘለንስኪ ለመውሰድ ቀዳሚ ናቸው እያሉ ነው።
በእስር ላይ የሚገኙት አሌክሲ ኔቫሊን አምናና ካቻምና የሩሲያ ተቃዋሚዎች በማሸነፋቸው ምንአልባትም እድላቸው ጠባብ ነው ተብሏል።
የኦስሎ የሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሄነሪክ ኦርዴል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የወጣበት 75ተኛ ዓመት በመሆኑ የሰላም ተሟጋቾች ሽልማቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
በኢራን በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት፣ የሴቶች መብት ተሟጋች እና የሞት ቅጣትን የሚቃወሙት ናርጅስ መሀመዲ ሽልማቱን ሊወስዱ እንደሚችሉም ተጠብቀዋል።
አፍጋኒስታናዊው ማህቡባ ሴራጅ የሴት ልጆች የትምህርት መብት እና ሌሎች የሴቶች መብቶች እንዲከበር በመስራት የኖቤል ሽልማትን በእጃቸው ሊያደርጉ ይችላሉም ተብሏል።
በሽህዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የኖቤል ሎሬቶችን ጨምሮ የም/ቤት አባላት፣ የዩኒቨርስቲ የታሪክ ወይም የህግ ፕሮፌሰሮች እጩዎችን መጠቆም ይችላሉ።