የኤለን መስክን ትኩረት ለማግኘት ኤክስን የጠለፈው “አኖኒመስ ሱዳን”
የመረጃ ጠላፊዎቹ የኤለን መስክ ኩባንያ ስታርሊንክ በሱዳን አገልግሎት እንዲሰጥ እንፈልጋለን ብለዋል
ኤለን መስክ ስለመረጃ ጠለፋውም ሆነ ስላነሱት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም
“አኖኒመስ ሱዳን” የሚል ስያሜ ያለው የመረጃ ጠላፊ ቡድን የኤለን መስኩን ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) መጥለፉን አስታወቀ።
በጠለፋው ምክንያት ኤክስ በበርካታ ሀገራት ለሁለት ስአታት አገልግሎቱ መስተጓጎሉ ተገልጿል።
ማክሰኞ ጠዋት የተከሰተው የመረጃ ጠለፋ በአሜሪካ እና ብሪታንያ ብቻ 20 ሺህ ሰዎች የማህበራዊ ትስስር ገጹን መጠቀም እንዳይችሉ አድርጎ እንደነበር ዳውንዲቴክተር የተሰኘው ተቋም አስታውቋል።
የመረጃ መንታፊው ቡድን አባላት “ኤለን መስክ ትኩረት እንዲሰጠንና በሱዳን ስታርሊንክን እንዲከፍት መልዕክት ለማስተላለፍ ነው የመረጃ ጠለፋውን ያካሄድነው” ብለዋል።
ቢቢሲ “ክሩሽ” ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር በቴሌግራም ባደረገው ቆይታ፥ ማክሰኞ እለት የኤክስ አገልግልሎት ለስአታት የተቋረጠው በአንድ ጊዜ በበርካታ አካውንቶች የመተግበሪያውን ትራፊክ በማጭናነቅ ስለመሆኑ ነግሮኛል ብሏል።
“ሆፋ” የሚል ስያሜ እንዳለው የገለጸ ሌላኛው የቡድኑ አባልም የመረጃ ጠለፋው አላማ አለም በሱዳን ስላለው የእርስ በርስ ግጭት ትኩረት እንዲሰጥ ለማሳሰብ ስለመሆኑ ገልጿል።
“አኖኒመስ ሱዳን” የት ይገኛል?
በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰሩ ተቋማት “አኖኒመስ ሱዳን” የሩሲያ የሳይበር ተቋም እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ገልጸዋል። ቡድኑ በሚያጋራቸው መረጃዎችም ለፕሬዝዳንት ፑቲን ያለውን ድጋፍ ማሳየቱን አንዱ አብነት አድርገው ያነሳሉ።
ይሁን እንጂ ቡድኑ ሩሲያ የምትዘውረውና የምትደግፈው እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል፤ የሚገኘውም በሱዳን መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ለቢቢሲ ልኳል።
“የረጅም ጊዜ እቅዳችን የሱዳን ህዝብ አሁን በፈተና ውስጥ ቢሆንም ምንም ነገር ለማድረግ የሚሳነው እንዳልሆነና በተለያዩ ዘርፎች ያለንን ልዩ ብቃት ለአለም ማሳየት ነው” ብሏል ክራሽ የተባለው የቡድኑ አባል።
በጥር ወር 2023 የተቋቋመው “አኖኒመስ ሱዳን” በፈረንሳይ፣ ናይጀሪያ፣ እስራኤልና አሜሪካ የሚገኙ በርካታ ተቋማትን ድረገጾች በመጥለፍ ስራቸውን ማስተጓጎሉ ተገልጿል።
በሱዳን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች ባሏት ኬንያ ላይም የሳይበር ጥቃት መፈጸማቸውና ከ5 ሺህ በላይ አገልግሎት የሚሰጠው “ኢሲቲዝን” የተሰኘ ፖርታል አገልግሎት እንዲያቆም ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የኤለን መስክ ኩባንያ ኤክስ በ”አኖኒመስ ሱዳን” ተፈጸመ ስለተባለው የመረጃ ጠለፋውም ሆነ ስላነሱት ስታርሊንክ በሱዳን የኢንተርኔት አገልግሎት ይጀምርልን ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የለም።