ቴሌግራም ለሳይበር ወንጀለኞች ጥቃት ተጋላጭ እየሆነ መጥቷል ተባለ
መተግበሪያው የሳይበር ወንጀለኞች የሚተራመሱበት ሌላኛው ‘ዳርክ ዌብ’ እየሆነ መጥቷልም ነው የተባለው
የተመዘበሩ ሚስጥራዊ መረጃዎችን የሚያጋሩ መረጃ በርባሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አንድ ጥናት አመልክቷል
ነጻ የኦንላይን መልዕክቶች መለዋወጫ መተግበሪያው ቴሌግራም ለሳይበር ወንጀለኞች ጥቃት ተጋላጭ እየሆነ መምጣቱን ጥናት አመለከተ፡፡
ቴሌግራም የተሰረቁ መረጃዎች መገበያያ ማዕከል እየሆነ መጥቷል ያለው ጥናቱ መተግበሪያው የሳይበር ወንጀለኞች የሚተራመሱበት ሌላኛው ‘ዳርክ ዌብ’ እየሆነ መጥቷል ብሏል፡፡
‘ዳርክ ዌብ’ ባለሙያዎች ብቻ ሊጠቀሙና ሊደርሱ የሚችሉበት ድብቅ የበይነ መረብ ግንኙነት ስፍራ ነው፡፡
‘ሳይበሪንት’ በተባለው የሳይበር ደህንነት ቡድን እና በፋይናንሽያል ታይምስ ጋዜጣ ትብብር የተካሄደው ጥናትም ቴሌግራም ለእንዲህ ዓይነት ባለሙያዎች ይበልጥ እየተጋለጠ መምጣቱን አረጋግጧል፡፡
የተሰረቁ መረጃዎችን ብዙዎች በሚጠቀሙበት በዚህ መተግበሪያ ላይ ለተዋቀሩና በሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ላሏቸው ቡድኖች የሚያጋሩ፣ለግዢ እና ሽያጭ የሚያቀርቡ በርካታ መረጃ መንታፊዎች (ሃከርስ) መኖራቸውንም ነው ጥናቱ ያመለከተው፡፡
ይህ ለአጠቃቀም ምቹ በሆነው ቴሌግራም ላይ ያሉ የቁጥጥር መንገዶች ከመላላታቸው የመጣ ነው እንደ አጥኚዎቹ ገለጻ፡፡
ከ47 ሺ በላይ አባላት ባሉት እና “ኮምቦ ሊስት” በተባለ አንድ ‘ፐብሊክ ቻናል’ ሃከሮች የይለፍ ቃላትን ጭምር የያዙ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ያፈተለኩ መረጃዎችን ለሽያጭ አቅርበዋል ሲሉም በማሳያነት ያስቀምጣሉ፡፡
ለክፍያ አገልግሎት የሚውሉ ካርዶች፣ የግለሰቦች የባንክ መረጃ እንዲሁም የፓስፖርት ቅጂዎች በመተግበሪያው መጠቀሚዎች ለሽያጭ ከሚቀርቡት መካከል ናቸው እንደ ዘገባዎች ገለጻ፡፡
የሰዎችን መረጃ ለመበርበር የሚያገለግሉ መተግበሪያዎች እና መመሪያዎች በወንጀለኞቹ እንደሚቀርቡም ጥናቱ አመልክቷል፡፡
አጥኚዎቹ “ቴሌግራም የሳይበር ወንጀለኞች መጠቀሚያ እየሆነ መምጣቱን በልበ ሙሉነት እንናገራለን” ብለዋል፡፡
በተለይ ሚስጥራዊ መረጃዎች የሚጋሩበት የመተግበሪያው የአገልግሎት ክፍል፤ የተሰረቁ መረጃዎችን በድብቅ መሸጥ ለሚፈልጉ ሃከሮች ይበልጥ እየተመቸ መምጣቱን ነው በሳይበሪንት የሳይበር አደጋዎች ተንታኙ ታል ሳምራ የተናገረው፡፡
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ስራ የጀመረው ቴሌግራም ለመለዋወጥ ምቹ እና ቀላል የሆኑ ነጻና ፈጣን የኦንላይን መልዕክቶች አገልግሎትን ይሰጣል፡፡ ከ500 ሚሊዬን የሚልቁ ተጠቃሚዎችም አሉት፡፡
ሆኖም የወንጀለኞቹ መበራከት መቀመጫውን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ አድርጎ በመስራት ላይ የሚገኘውን ተቋም በአሰራሮቹ ላይ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ሊያስገድዱት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡