ትውልደ ግብፃዊው አይመን አል ዘዋሂሪ፤ ኦሳማ ቢላደንን በመተካት አል ቃይዳን ሲመራ ነበር
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአልቃይዳ መሪ አይማን አል ዘዋሂሪን እንደተገደለ መናገራቸው ይታወሳል።
የሽብር ቡድኑ መሪ፤ የአሜሪካ የስለላ ተቋም (ሲአይ ኤ) በፈጸመው የድሮን ተልዕኮ መገደሉን ጆ ባይደን አረጋግጠዋል።
የቀድሞውን መሪ ኦሳማ ቢላደንን በመተካት አል ቃይዳን ሲመራ የነበረው ትውልደ ግብፃዊው አይመን ዘዋሂሪን የተገደለው በአፍጋኒስታን ካቡል መሆኑንም ጆ ባይደን ተናግረዋል።
አይማን አል ዘዋሂሪን የተገደለው የሽብር ቡድኑን ቁልፍ መሪዎችን ኢላማ በማድረግ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት እንደሆነም ተገልጿል።
የአል ዘዋሂሪን መገደልን ተከትሎ በቀጣይ የሽብር ቡድኑን ማን ይችላል በሚል የተለያዩ መላምቶች በመነሳት ላይ ናቸው።
አሁን ላይ እየወጡ ባሉ መረጃዎች ሌላኛው ግብጻዊ ሰይፍ አል ማስሪ ሊተካ እንደሚችል ግምቶች በመውጣት ላይ ናቸው።
ይህ ግብጻዊ በኢራን በረሀማ ስፍራዎች ውስጥ ተሸሽጎ እንዳለ የሚገመት ሲሆን ሟቹ የአልቃይዳ መሪ አይመን አልዘዋሪን ሊተካ ይችላል ተብሏል።
ሰይፍ አል ማስሪ ላለፉት 30 ዓመታት በአልቃይዳ የሽብር ቡድን ውስጥ የተለያዩ ተልዕኮዎችን ሲመራ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን የሽብር ቡድኑን ከዚህ በፊት ኦሳማ ቦንላደን በነበሩበት ጊዜ ወደ ነበረበት ቁመና ሊመልሰው እንደሚችል ተሰግቷል።
አልማስሪ በፈረንጆቹ 1998 ናይሮቢ በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ላይ የተፈጸመውን እና ለ224 ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነውን የሽብር ድርጊት በመምራት ይፈለጋል።
አሜሪካ ይሄን የሽብር ቡድን መሪ ለያዘ ፣ለገደለ ወይም ለጠቆመ ግለሰብ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል ይፋ አድርጋለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት፤ አል ቃይዳ መሪ መገደሉ፤ የቱንም ያህል ጊዜ ቢወስድም በመስከረም 11 ጥቃት የተጎዱት ዜጎች ፍትህ ማግኘታቸውን ያመለክታል ብለዋል።
ባይደን፤ የቡድኑ መሪ አይማን አል ዘዋሪ እንዲደመሰስ ላደረጉ የሀገራቸው የጸጥታ ኃይሎች ምስጋና አቅርበዋል።
ባይደን በካቡል በተደረገው ጥቃት ንጹኃን ኢላማ እንዳልተደረጉ ቢገልጹም ታሊባን ግን አጣጥሎታል።
በአፍጋኒስታን የተደረገውንና የአል ቃይዳ መሪ የተገደለበትን ጥቃት ታሊባን አውግዞታል።
የወቅቱ የአፍጋኒስታን ገዥ ታሊባን፤ አሜሪካ ጥቃት ያደረሰችው በመኖሪያ ቤት አካባቢ ነው ብሏል።