ፕሬዝዳንት ባይደን ጉዳዩን በማጤን ላይ ነን ብለዋል
በየመን የሚንቀሳቀሰውን የሃውሲ አማጺ ቡድን በድጋሚ በሽብርተኝነት ስለመፈረጅ እያጠየኑ እንደሆነ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ፡፡
“አዎ፤ ጉዳዩን በማጤን ላይ ነን” ብለዋል ባይደን የስልጣን ዘመናቸውን አንደኛ ዓመት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
በየመን ያለውን ጦርነት ለማቆም የጦርነቱን ተሳታፊ አካላትን ጭምር የሚመለከት በመሆኑ ቀላል እንደማይሆን ባይደን ተናግረዋል፡፡
የሃውሲ አማጽያን ባሳለፍነው ሰኞ ንጹሃን ዜጎችንና መገለገያዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃትን በአቡ ዳቢ ፈጽመዋል፡፡
በጥቃቱ ሁለት ህንዳውያን እና አንድ ፓኪስታናዊ በድምሩ ሶስት ንጹሃን ተገድለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን በጽኑ እንዲያወግዝና እርምጃ እንዲወስድ ጠይቃ ነበረ፡፡
በአሜሪካ የዩኤኢ አምባሳደር ዩሱፍ አል ኦታይባም የባይደን አስተዳደር በንጹሃን ላይ እንዲህ ዐይነት አረመኔያዊ ድርጊት የፈጸመውን ቡድን በድጋሚ በሽብርተኝነት እንዲፈርጅ ጠይቀዋል፡፡
የአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድም ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊሎድ ኦስቲን ጋር የአማጽያኑን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል “ቆራጥ ዓለም አቀፋዊ አቋም” መያዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ረቡዕ አውርተዋል፡፡
ዛሬ ወደ እንግሊዝ እንደሚያቀኑ የተነገረላቸው የፕሬዝዳንት ባይደን የየመን ልዩ መልዕክተኛ ቲም ሊንደርኪንግ የባህረ ሰላጤው ሃገራትን እንደሚጎበኙ ተሰምቷል፡፡ ሆኖም ጉብኝቱ በዋናነት በየመን ተኩስ ለማቆም በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር እንደሆነ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሃውሲ አማጽያንን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ ወስነው ነበር፡፡ ሆኖም ውሳኔው ትራምፕን አሸንፈው ወደ ስልጣን በመጡት በፕሬዝዳንት ባይደን ተሰርዟል፡፡
እስካሁን በአማጺ ቡድኑ መሪዎች ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣልም ነበር የተቆየው፡፡ ሆኖም የሰሞኑን ጥቃት ተከትሎ ቡድኑን በሽብርተኝነት ስለ መፈረጅ በማጤን ላይ መሆናቸውን ባይደን አስታውቀዋል፡፡