ሽብርተኞችን ትደግፋለች ያሉ ቡርኪናውያን የፈረንሳይ የጦር ተሽከርካሪዎችን አገቱ
የሽብር ጥቃቶች በመጨመራቸው የተማረሩት የአካባቢው አገራት ዜጎች ፈረንሳይ ጦሯን እንድታስወጣ በመጠየቅ ላይ ናቸው
የጦር ተሽከርካሪዎቹን ያገቱ የካያ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው
የቡርኪና ፋሶዋ ካያ ከተማ ነዋሪዎች የፈረንሳይ የጦር ተሽከርካሪዎችን አገቱ፡፡
ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ቡርኪናፋሶ በተደጋጋሚ በአክራሪ የሽብር ቡድኖች ጥቃት እየደረሰባት ሲሆን የአገሪቱ ጦር ጥቃቱን ማስቆም አልቻለም፡፡
የፓን አፍሪካኒስቱ ቶማስ ሳንካራ አገር ዜጎች በሽብር ቡድኖች ጥቃት ምክንያት መኖሪያ ቀያቸውን በመልቀቅ ለከፋ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡
ቡርኪናፋሶን ጨምሮ በምዕራብ አፍሪካ በአክራሪ ጽንፈኞች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመሩ ሲሆን ፈረንሳይ ጥቃቶቹን ለማስቆም በሚል ጦሯን ወደ አካባቢው ልካለች፡፡
ይሁንና ጥቃቶቹ እየጨመሩ በመምጣታቸው የተማረሩት የአካባቢው አገራት ዜጎች ፈረንሳይ ጦሯን እንድታስወጣ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የቡርኪናፋሶዋ ካያ ከተማ ነዋሪዎችም የፈረንሳይ ጦር ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ወደ ጎዳናዎች በመውጣት መንገድ ዘግተዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፈረንሳይ በሩዋንዳው ዘር ጭፍጨፋ ‘የጎላ ሚና’ እንደነበራት የሚያመለክት የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ
ነዋሪዎቹ እንዳሉት የፈረንሳይ ጦር በአገራቸው ከሚንቀሳቀስ ይልቅ ወደ አገሩ ቢመለስ ምርጫቸው ነው፡፡
የፈረንሳይ ጦር ተሽከርካሪዎቹ ከቡርኪናፋሶዋ ካያ ከተማ ወደ ኒጀር የማለፍ እቅድ የነበረው ሲሆን እቅዱ በከተማዋ ነዋሪዎች መስተጓጎሉ ተገልጿል፡፡
ነዋሪዎቹ ጽንፈኞች ቡርኪናፋሶን እና በአካባቢው ያሉ አገራትን እንዲያጠቁ የፈረንሳይ ጦር ድጋፍ እያደረገ ነው እያሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲናገሩ እንደነበርም ዘገባው አክሏል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች በቡርኪና ፋሶ ጦር ላይ በከፈቱት ጥቃት 49 ወታደሮች መገደላቸው ይታወሳል፡፡
በአገሪቱ መዲና ያለው የፈረንሳይ ኢምባሲ እና የፈረንሳይ ጦር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ መስጠት እንዳልቻለ ዘገባው ጠቅሷል፡፡
የማሊ መንግስት ከጽንፈኛ ሀይሎች ጋር የተጀመረውን ዉጊያ ለመመከት ከሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር ንግግር መጀመሩን ተከትሎ ፈረንሳይ መበሳጨቷ እና እቅዱ ተቀባይነት የለውም ብሄራዊ ጥቅሜንም ይጎዳል ማለቷ ይታወሳል፡፡
ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ከ3 ሺህ በላይ ጦር ማሰማራቷ የተገለጸ ሲሆን የተወሰኑ የአካባው አገራት አገሪቱ ጦሯን እንድታስወጣ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡