ሊጉ አማጽያኑ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ስጋት መሆናቸውን አስታውቋል
የአረብ ሊግ በየመን የሚንቀሳቀሱት የሃውሲ አማጽያን በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ጠየቀ፡፡
ሊጉ አማጽያኑ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመፈጸም ላይ ያሉትን የሽብር ጥቃት በማውገዝ ትናንት እሁድ በግብጽ ካይሮ አስቸኳይ ስብሰባን አድርጓል፡፡
በስብሰባው ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የሚጥስ ነው ያለው ሊጉ የሲቪል እና የኢነርጂ ተቋማትን ዒላማ ማድረጋቸው የዓለምን የንግድ ሚዛን የሚያዛባ ነው ሲል አስታውቋል፡፡
“ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ስጋት ከመሆናቸውም በላይ የመላው አረብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው” ሲልም ነው ቀጣናዊው ተቋም መግለጫ ያወጣው፡፡
በአስቸኳይ ስብሰባው የዩኤኢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ኸሊፋ ሻሂን አል መራር ተሳትፈዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ወሳኝ” እርምጃዎችን ካልወሰደ አማጽያኑ አሁንም በየመን ህዝብና መንግስትም ላይ ሆነ በቀጣናው ሃገራት ላይ ጥቃቶችን ከመፈጸም እንደማይቦዝኑ አሳስበዋል፡፡
ሃገራቸው ራሷን የመጠበቅ ህጋዊም ሞራላዊም መብት እንዳላትም ነው ሚኒስትር ዴዔታው የተናገሩት፡፡
“በሽብርተኝነት የምንታመስበትን ሁኔታ አንታገስም” ሲሉም አስቀምጠዋል፡፡
አማጽያኑ በወቅቱ የሊጉ ሊቀመንበር ኩዌት የተጠራውን ይህን አስቸኳይ ስብሰባ ተከትሎ የሚሳዔል ጥቃትን በአቡ ዳቢ ፈጽመዋል፡፡ ሆኖም ጥቃቱ አንዳች ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ጉዳት ሳያደርስ ማምከን መቻሉን የዩኤኢ መከላከያ አስታውቋል፡፡
በሃውሲ የተፈጸመውን ይህን ጥቃት ተከትሎ የተለያዩ ሃገራት ድርጊቱን እያወገዙ ነው፡፡ ከዩኤኢ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ የጥቃቱ ዒላማ ከሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ጎን መቆማቸውን፤ ያላቸውንም አጋርነት እየገለጹ ነው፡፡
ባህሬይን፣ ኩዌት፣ ግብጽ፣ ቱርክ እና ዮርዳኖስ ድርጊቱን በጽኑ አውግዘዋል፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒቴሮቻቸው በኩል ባወጡት መግለጫ፡፡
የፈሪዎች ባሉት በዚህ ጥቃት ማዘናቸውን ከመግለጻቸውም በላይ ድርጊቱ ከዓለም አቀፍ ህግጋት የሚጻረር መሆኑን በማስታወስ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዩን በቸልታ ሊያውት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
ሃውሲዎች ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ በአቡ ዳቢ በፈጸሙት ተመሳሳይ የባሊስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ሶስት ሰዎችንን መግደላቸው እና ስድስት ገደማ ሰዎችን መጉዳታቸው እንዲሁም በሲቪል መገልገያ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሃገራትና አፍሪካ ኅብረትን መሰል አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሽብር ድርጊቱን ማውገዛቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ አማጽያኑን በሽብርተኝነት ስለ መፈረጅ በድጋሜ ለማሰብ መገደዷን ማስታወቋም አይዘነጋም፡፡