የተመድ ዋና ጸሃፊ “በለጸጉ ሀገራት ቃላቸውን ባለማክበራቸው ዓለማችን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባታል” አሉ
ጉቴሬዝ "፤ ጣት ሳንቀሳሰር ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅብናል” ብለዋል

27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በመጪው ወርሃ ህዳር በግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል
የበለጸጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የገቡትን ቃል ለመተግበር በመዘግየታቸው ዓለማችን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባታል ሲሉ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናገሩ።
በፓሪሱ ጉበዔ የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም በቃላቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ቆይቷል።
በዚህ ስጋት የገባቸው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ዓለም ወደ ተግባር ካልገባ የሚመጣው አደጋ ከዚህም የባሰ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የፓኪስታን አንድ ሶስተኛ ክፍል በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአውሮፓ በ500 ዓመታት ውስጥ ያጋጠመው የበጋ ወቅት እንዲሁም መላው ኩባ እና አሜሪካ ኢያን እየደረሰ ያከው የአውሎ ነፋስ አደጋ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች ናቸው ያሉት ዋና ጸኃፊው፤ ችግሩን ለመቅረፍ የሚወሰዱ እርመጃዎች በቂ አይደሉም ሲሉ ተናግረዋል።
“የአየር ንብረት ትርምስ ወደፊት እየገሰገሰ ቢሆንም የሚወሰደው እርመጃ ቆሟል” ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ በመጪው ህዳር ወር በግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ ከተማ ስለሚዘጋጀው 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን በማስመለከት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ።
አሁን ያሉት ቃል ኪዳኖች እና ፖሊሲዎች የዓለምን የሙቀት መጠን 1.5 ዲግሪ ማሟላት ይቅርና ወደ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ እያለ ነው ስለዚህም የነገ ህይወታችን አጠያያቂ ነውም ብለዋል።
እናም ቀጣዩ ጉባዔ (ኮፕ-27) ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስሚወሰደው እርምጃ ቅድሚያ ሰጥተው የሚመክሩበት ወሳኝ ጉባኤ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ዋና ጸሃፊው፤ "የልቀት መጠኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ነው፤ ጣት ሳንቀሳሰር መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅብናል” ሲሉም አሳስበዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፤ ዓለማችን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺዬስ ገዳማ ጨምራለች። ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠንም በ50 በመቶ ጨምሯል።