ከሂዝቦላህ ወደ እስራኤል የተተኮሰ ሚሳኤል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጉዞን አስተጓጎለ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤልን እየጎበኙ ነው
ሚሳኤል ከሂዝቦላህ ወደ እስራኤል መተኮሱን ተከትሎ አንቶኒ ብሊንከን እና ቡድናቸው እንቅስቃሴዎቻቸው ተስተጓጉሏል
ከሂዝቦላህ ወደ እስራኤል የተተኮሰ ሚሳኤል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጉዞን አስተጓጎለ።
የፍልስጤሙ ሐማስ ከአንድ ዓመት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረው ጦርነት መቋጫ አላገኘም።
አድማሱን እያሰፋ የመጣው ይህ ጦርነት የእስራኤል ጦር ወደ ሊባኖስ በመግባት ከሂዝቦላህ ተዋጊዎች ጋር እየተዋጉ ናቸው።
በምድር እና አየር ላይ ጥቃቶች ታግዞ የቀጠለው ይህ ጦርነት እንዲቆም አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት አሳስበዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤል እና ሂዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ በሚል ወደ ቴልአቪቭ አቅንተዋል።
ሚንስትሩ በእስራኤል በስራ ላይ እያሉ ከሂዝቦላህ የተተኮሰ ሚሳኤል ወደ እስራኤል የአየር ክልል መግባቱን ተከትሎ የማስጠንቀቂያ ደወል ተደውሏል።
በዚህ ጊዜም አንቶኒ ብሊንከን እና ቡድናቸው ራሳቸውን ከሚሳኤል ጥቃት ለመጠበቅ መሸሸጊያ ሲፈልጉ ታይተዋል።
የእስራኤል ጦር ከሂዝቦላህ የተተኮሰውን ሚሳኤል አቅጣጫ አስቀይሮ በባዶ ቦታ እንዲያርፍ ያደረገ ቢሆንም የአንቶኒ ብሊከን ጉዞ ግን እንደተስተጓጎለ ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የሂዝቦላህ ሚሳኤል ሚንስትሩ ብሊንከን ወደ ኤርፖርት ሊጓዙ የነበራቸውን እቅድ እንዲያዘገዩ አስገድዷቸዋል።
እስራኦል ከሊባኖስ በተጨማሪ በጋዛ እያደረገች ያለችውን ጥቃት ያጠናከረች ሲሆን በተለይም ከሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደል እና ከእስራኤል አዋጊ ኮለኔል መገደል በኋላ ከባድ ድብደባ እያካሄደች ትገኛለች።
አሜሪካ በበኩሏ እስራኤል በጋዛ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በአንድ ወር ውስጥ ካላሻሻለች የጦር መሳሪያ ድጋፏን ልታቋርጥ እንደምትችል አስጠንቅቃለች።