እስራኤል የሂዝቦላህ መሪዎችን መግደሏ የተሻለ ሰላም ይሰጣታል?
እስራኤል መስከረም ወር ውስጥ ብቻ ከአምስት በላይ የሂዝቦላህ ከፍተኛ መሪዎችን ገድላለች
የቡድኑ ዋና መሪ ሀሰን ናስራላህ ከትናንት በስቲያ በቤሩት መገደላቸው ይታወሳል
እስራኤል የሂዝቦላህ መሪዎችን መግደሏ የተሻለ ሰላም ይሰጣታል?
እስራኤል ባሳለፍነው አርብ ሌሊት በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሀሰን ናስራላህን መግደሏ ይታወሳል።
የሄዝቦላህ መሪው ሀሰን ናስራላህ እስራኤል በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት መገደላቸውን ባወጣው መግለጫ አረጋገጧል።
ይህን ተከትሎ የተወሰኑ ሀገራት የእስራኤልን ድርጊት ደግፈው አስተያየት ሲሰጡ የተወሰኑት ደግሞ ግድያውን አውግዘዋል።
በርካታ የዓለማችን ሀገራት ደግሞ እስራኤል የሂዝቦላህ አመራሮችን ስለገደለች የተለየ ደህንነት ልታገኝ እንደማትችል በመናገር ላይ ናቸው።
ጀርመን እስራኤል የተሻለ ደህንነት እና ከጥቃት መዳን የምትችለው ከሂዝቦላህ ጋር በመደራደር የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈጸመች መሆኑን አስታውቃለች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አናሌና ባርቦክ እንዳሉት እስራኤል ቤሩት ላይ ጥቃት በማድረስ የሂዝቦላህ መሪዎችን ኢላማ ስላደረገች ዘላቂ ሰላም አታገኝም ብለዋል።
የእስራኤል ጥቃት የአካባቢውን ደህንነት ወደ ተባባሰ ጦርነት እና አለመረጋጋት ሊመራው ይችላል ስትል ማስጠንቀቋን አናዶሉ ዘግቧል።
ከጀርመን በተጨማሪ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ሌሎችም የአረብ ሀገራት እስራኤል እና ሂዝቦላህ የሶስት ሳምንታት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሀሰን ናስራላህ ግድያ ፍትሀዊ እርምጃ ነው ሲሉ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ ግድያውን አውግዘዋል።