የዓለም ፍጻሜ ደርሷል በሚል ከኡጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ መጡ ስለተባሉት ሰዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን አለ?
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ እንደሆነ ተገልጿል
የተመድ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች መርማሪ ቡድን የቆይታ ጊዜ እንዲቋረጥ ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላትም በሳምንታዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ተነስቷል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የአሜሪካ እና ኢትዮጵያን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያሳድገው ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር መለስ አለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ያነሱት።
የዓለም ፍጻሜ ዱርሷል በሚል ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ስለተባሉት ኡጋንዳዊያን፣ ስለ ተመድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ፣ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዓረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ስላሰሙት ንግግር እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ቃል አቀባዩ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ከሰሞኑ ከ100 በላይ ኡጋንዳዊያን የዓለም ፍጻሜ ደርሷል ፣መድህን የሚገኘውም በኢትዮጵያ ነው በሚል ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ስለተባሉት የሀይማኖት ሰዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ዜናውን እንደሰሙት የተናገሩት አምባሳደር መለስ "በተባለው ልክ ከኡጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የሚያሳይ ነገር የለም፣ ከወትሮው የተለየ ቁጥር ያላቸው ኡጋንዳዊያን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የሚያሳይ ነገር የለም" ብለዋል።
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሽኩሪ በአረብ ሊግ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተናጠል እርምጃ እየወሰደች እንደሆነ መናገራቸውን አምባሳደር መለስ ተችተዋል።
ቃል አቀባዩ "የግብጽ አቋም ኋላቀር እና ጊዜውን የማይመጥን ነው፤ ስለ ህዳሴው ግድብ አሁን ላይ መናገር የሚያስችል ምንም አዲስ ነገር የለም፤ ግንባታው በራስ ሀብት ህዝብን ለመጥቀም ተብሎ የተጀመረ እና አሁንም የቀጠለ ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ምርመራ የባለሙያዎች ቡድን ዓላማው ፖለቲካዊ ስለሆነ ቆይታው እንዲቋረጥ ኢትዮጵያ ትፈልጋለችም ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።