በጸረ-አፓርታይድ ትግል የሚታወቁት የደቡብ አፍሪካው ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 አመታቸው አረፉ
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የዴዝሞንድ ቱቱን ህልፈት"ለደቡብ አፍሪካውያን ትውልዶች ሌላው የሀዘን ምዕራፍ ነው" ሲሉ ገልጸውታል
የዴዝሞንድ ቱቱ በአፓርታይድ ላይ ባደረጉት ሰላማዊ ተቃውሞ እንደፈረንጆቹ በ1984 የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸው ይተዋሳል
በደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ዘመቻ ጉልህ ሚና የነበራቸው ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ፤ ህይወታቸው ያለፈው ከካንሰር በሽታ ጋር ሊሆን እንደሚችልም ነው የሊቀ ጳጳሱ ጽ/ቤት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቱቱ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለባቸው አውቀው የነበረ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከካንሰር ህክምናው ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎችን በበርካታ አጋጣሚዎች ሆስፒታል ሲመላለሱ ቆይቷል፡፡
የሊቀ ጳጳሱ ዴዝሞንድ ቱቱ ተጠባባቂ ሰብሳቢና የሊቀ ጳጳሱ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶክተር ራምፌሌ ማምፌላ የቱቱ ቤተሰብን ወክለው በሰጡት መግለጫ "በመጨረሻም ቱቱ በ90 አመቱ ዛሬ ጥዋት በኬፕ ታውን ኦሲስ ፍራይል የእንክብካቤ ማእከል በሰላም አረፉ" ሲሉ ተናግሯል፡፡
ዶክተሯ የቱቱን ማለፍ ይፋ ቢያደርጉም የማቹ መንስኤን በተመለከተ ዝርዝር ነገር ከመናገር ተቆጥቧል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ህልፈት በሀገራችን ነጻ የወጣችውን ደቡብ አፍሪካን ውርስ ለሰጡን ደቡብ አፍሪካውያን ትውልዶች ሌላው የሀዘን ምዕራፍ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በአፓርታይድ ላይ ባደረጉት ሰላማዊ ተቃውሞ እንደፈረንጆቹ በ1984 የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፍ የቻሉት ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ፤ ከአስር አመታት በኋላም የዚያን የጨለማ ዘመን ግፍና በደል በቁፋሮ ለማውጣት የተቋቋመ የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን ሊቀመንበር በመሆን የዚያን አገዛዝ መጨረሻ መመልከት የቻሉ ታላቅ ሰው እንደነበሩ ይታወሳል፡፡