በ2016 በጀት አመት ሊመዘበር የነበረ 2.8 ቢሊየን ብር ማዳኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ
ሀብታቸውን ማስመዝገብ ከሚኖርባቸው ከ2 ሚለየን በላይ በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ አመራሮች እና ተመራጮች 175 ሺህ ያህሉ ማስመዝገባቸው ተሰምቷል
ከዛሬ ሶስት አመት በፊት ከስራ አጥነት እና ኑሮ ውድነት ቀጥሎ ሙስና በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝ ማህበራዊ ችግር እንደነበር ይታወሳል
በ2016 በጀት አመት ሊመዘበር የነበረ 2.8 ቢሊየን ብር ማዳኑን የፌደራል ስነምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽኑ አስታወቀ።
ዜጎች ከመንግስት ማግኝት ላለባቸው አገልግሎት የሚጠየቁት እጅ መንሻ ወይም ጉቦ የመልካም አስተዳደርን ከማበላሸት ባለፈ ተገቢ ያልሆነ ሀብትን በማከማችት በሰዎች መካከል ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠሩ ከሚያደርጉ ማህበራዊ ጠንቆች መካከል ነው፡፡
በተለያዩ የፌደራል እና የመንግስት ተቋማት ጉዳዮችን ለማስፈጽም በሚጠየቁ ያልተገቡ ክፍያዎች የተማረሩ ዜጎችም በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡
ከዛሬ ሶስት አመት በፊት ከስራ አጥነት እና ኑሮ ውድነት ቀጥሎ ሙስና በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝ ማህበራዊ ችግር እንደነበር ይታወሳል፡፡
የፌደራል ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በተጠናቀቀው በጀት አመት ሙስናን ለመከላከል በምስራው ስራ 2.8 ቢሊየን ብር ማዳን ችያለሁ ብሏል፡፡
በኮሚሽኑ የኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋየ ሻሜቦ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት የሙስና አይነት በየጊዜው እየተቀያየረ ይገኛል፡፡
ተቋሙ “የአስቸኳይ ሙስና መከላከል” በተባለ አሰራር ሙስና ከመፈጸሙ በፊት ለማስቆም የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም በአመቱ ሊመዘበር የነበረ 2.8 ቢሊየን ብር እና 8,490 ዶላር የሕዝብና የመንግሥት ሀብትና ንብረት ማዳን መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም በዘንድሮ በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 6,565 የሙስና ወንጀል ጥቆማ ከህዝቡ ለኮሚሽኑ የደረሰ ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ 2,123 ለተጨማሪ ምርመራ ለፍትሕ አካላት የተላከ መሆኑን ተናረዋል፡፡
የገጠር እና የከተማ መሬትን በተመለከተ በአመቱ 46,467ካሬ ሜትር በላይ የከተማና የገጠር መሬት በሙስና ሊጭበረበር ሲል ደርሰንበታል ነው ያሉት፡፡
ኮሚሽኑ አሰራራቸው ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ ዘርፎች እና ተቋማት ላይ የአሰራር መሻሻያዎች ተግባራዊ እንዲያደረጉ ለማሳሳብ እያከናወነ የሚገኝውን ጥናት በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ተስፋየ፤ የገቢ ግብር እና ታክስ አሰባሰብ ፣ የጉምርኩ አሰራር እና ኮንትሮባንድ ፣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ፣ ወደ ውጭ ሀገራት በሚላኩ ሰራተኞች ስምሪት እና በመሬት አስተዳደር ጥናት ከሚካሄድባቸው ተቋማት መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
የመንግስት ንብረት ግዢ ፣ መሬት አስተዳደር እና ፈቃድ አሰጣጥ ፣ ገቢ እና ታክስ አሰባሰብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የሙስና ጥቆማዎች ከሚቀርቡባቸው ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የመንግስት ሀላፊዎች እና አመራሮችን ሀብት ምዝገባ በተመለከተ ምዝገባው ከተጀመረበት 2003 ዓም ጀምሮ በአጠቃላይ ከ175ሺህ 627 በላይ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የቡድን መሪዎችን ሀብት እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የመንግስት ሀላፊዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የሕዝብና መንግሥት ሀብት ላይ የመወሰን እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት ገንዘብ ላይ የማዘዝ ሥልጣን አላቸው ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡
በክልል እና በፌደራል ደረጃ ሀብቱን ማስመዝገብ የሚኖርበት ሃላፊ ፣ ተመራጭ፣ ተሿሚ፣ እንዲሁም ሠራተኛ ቁጥር በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንደሚሆንም ነው የተሰማው፡፡
በፌዴራል ደረጃ ሀብታቸውን ካስመዘገቡ መካከል በአመቱ 113 አመራሮች ላይ የሀብት ማጣራት ሥራ ተካሂዷል፡፡
በኮሚሽኑ የኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋየ ሻሜቦ ሀብት ከመንግስት ሃላፊዎች ሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ በክልሎች አካባቢ የሚገኙ አመራሮች ወደ ፊት በሙስና ላገኝው እኘላለሁ የሚሉቱን አሁን የሌላቸውን ሀብት የማስመዝገብ ሙከራ እንደሚያጋጥም ነግረውናል፡፡
ሙስናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህዝብ ጥቆማ ወሳኝ ነው ያሉት የኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ሀላፊው ህዝቡ መብቱን በገንዘብ ከመግዛት መቆጠብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በቅርብ አመታት ጥቆማ በመስጠት ደረጃ የተሸሻሉ ነገሮች ቢኖሩም አሁንም ግን ህብረተሰቡ ሙስና በሚጠየቅበት ጊዜ ከተቻለ በማስረጃ ካልሆነም ጥቆማውን ለኮሚሽኑ ቢያቀርብ አስፈላጊውን ማሻሻያ እና ተጠያቂነት ለማስፈን ያግዛል ብለዋል
ህብረተሰቡ ጥቆማ የሚያቀርብባቸውን አማራጮች ለማስፋትም ኮሚሽኑ በቅርቡ ወደ ስራ የሚያስገባቸው ከአርቲፊሻል ኢንተለጄንስ ተቋም ጋር በተመባበር ሶፍትዌር እና መተግበርያዎችን በማበልጸግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሙስናን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም አሁን ካለበት ደረጃ ግን በእጅጉ መቀነስ ይቻላል ያሉት ሃላፊው ከሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን በርካታ የመንግስት አሰራሮች በቴክኖሎጂ ወደ ታገዘ አሰራር በመቀየር መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡