አሀዛዊ መረጃዎች ስለ ትራምፕ እና ባይደን የምርጫ ፉክክር ምን ይናገራሉ?
ባይደን ከእጩነት እራሳቸውን እንዲያገሉ የሚፈልጉ የዴሞክራት ደጋፊዎች ቁጥር 54 በመቶ ተሻግሯል
ዶናልድ ትራምፕ ያላቸው ህዝባዊ ተቀባይነት 52 በመቶ መድረሱ ተገልጿል
አሀዛዊ መረጃዎች ስለ ትራምፕ እና ባይደን የምርጫ ፉክክር ምን ይነግራሉ።
በርካታ ውዝግቦችን እያስተናገደ በሚገኝው የ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፣ ምርጫውን ማን ያሽንፋል ከሚለው ጥያቄ እኩል የዴሞክራቱ ዕጩ ጆ ባይደን በምርጫው የመቀጠላቸው ነገር መነጋገርያ ሆኗል፡፡
ከፍተኛ የፉክክር መንፈስ ባላቸው ሁለቱ እጩዎች መካከል የሚደረገው ትንቅንቅ አሜሪካ እና አለም አሁን ከምትገኝበት ሁኔታ ጋር ተዳምሮ የምርጫውን ውጤት እና ከዛ በፊት ያሉ ሂደቶች የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ስቧል፡፡
አሀዛዊ መረጃዎች በሁለቱ እጩዎች መካከል ያለውን ህዝባዊ ተቀባይነት እና የአሸናፊነት እድላቸውን በመወሰን ደረጃ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በተለያዩ ድርጅቶች የሚሰባሰቡ ህዝባዊ አስተያየቶች እጩዎቹ ያሉበትን ደረጃም የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
በሰኔ ወር እስከተካሄደው የመጀመርያ ዙር የምርጫ ክርክር ድረስ ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራም ያላቸው ተቀባይነት ተቀራራቢ በሚባል ደረጃ ነበር፡፡
ክርክሩ ከመካሄዱ በፊት በተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች ትራምፕ 50 ባይደን ደግሞ 48 በመቶ ተቀባይነት እንዳላቸው የሚያመላክቱ ነበሩ፡፡
የዴሞክራቱ እጩ ነጥብ ጥለውበታል ከተባለው ክርክር በኋላ ግን ትራምፕ ያላቸው ተቀባይነት ሲያድግ በአንጻሩ ባይደን ከዴሞክራት እጩነት እንዲነሱ የሚጠይቁ ደምጾች በርክተዋል፡፡
ክርክሩ ከመካሄዱ በፊት ባይደን ከእጩነት እንዲነሱ የሚፈልጉ ሰዎች መጠን 19 በመቶ ብቻ የበረ ሲሆን ከክርክሩ በኋላ እስከ ትላንት ከሰአት ድረስ የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች 84 በመቶ አሜሪካውያን የባይደንን ከእጩነት መነሳት የሚፈልጉ ናቸው ተብሏል፡፡
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከተቃጣው የመግደል ሙከራ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ያላቸው ተቀባይነት ሲጨምር ባሳለፍነው እሮብ በኮቪድ 19 መያዛቸው የተሰማው ባይደን ደግሞ ምልክቶች በሙሉ የባይደንንን ለፕሬዝዳንት በቁ አለመሆን አመላካች ናቸው እንዲባል አድርጓል፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ የግድያ ሙከራውን ተከትሎ ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት ትራምፕ 52 በመቶ ተቀባይነት ሲያገኙ ባይደን ደግሞ 47 በመቶ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ በየሳምንቱ ከሚመዘገቡ አሜሪካውያን መራጮች ዘንድ ባላቸው ድጋፍ ትራምፕ በአራት ነጥብ እየመሩ ነው፡፡
በተጨማሪም ኤቢሲ ኒውስ በባይደን ደጋፊዎች ዙርያ ባሰባሰበው ድምጽ 54 በመቶዎች ፕሬዝዳንቱ ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ሲፈልጉ 81 በመቶዎቹ ደግሞ ለሌላ ስልጣን ዘመን አሜሪካን ለማስተዳደር ብቁ ናቸው ብለው እንደማያምኑ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
የምርጫ አሸናፊነትን በተመለከተ ትራምፕ እንደሚያሸነፉ 66 በመቶ አሜሪካውያን እምነት አላቸው፡፡
ባይደን እሺ ብለው ከእጩነት እራሳቸውን የሚያገሉ ከሆነ ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ የእርሳቸውን ቦታ ተክተው የዴሞክራት እጩ የመሆን እድላቸው 18 በመቶ ሆኗል፡፡
ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት የሚሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች የምርጫ አሸናፊውን ቅድመ ግምት ለማስቀመጥ እና እጩዎቹም አካሄዳቸው ላይ ለውጥ እንዲያደርጉ ወሳኝ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ከተሰበሰበው የህዝብ ድምጽ በተቃራኒ የምርጫ ውጤት ሲመዘገብም ይስተዋላል፡፡
ለአብነት በ2016 ምርጫ ሄላሪ ክሊንተን ትራምፕን ሊያሸነፉ እንደሚችሉ ከህዝብ አስተያየት በመነሳት የተሰጣቸው ግምት 90 በመቶ ቢሆንም በምርጫው በትራምፕ መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡