የሩሲያ ፍርድ ቤት በአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ላይ የ16 አመት እስር ቅጣት አስተላለፈ
የሩሲያ ፍርድ ቤት በስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ባለው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ላይ የ16 አመት እስር ቅጣት አስተላለፈ
የጋዜጠኛው ቀጣሪ ድርጅት የሆነው ዎል ስትሬት ጆርናል ፍርዱን "አሳፋሪ ፍርድ" ሲል አጣጥሎታል
የሩሲያ ፍርድ ቤት በአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ላይ የ16 አመት እስር ቅጣት አስተላለፈ ።
የሩሲያ ፍርድ ቤት በስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ያለውን አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ኢቫን ገርሽኮቪችን ለ16 አመታት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደርግበት እስር ቤት እንዲቆይ ቅጣት አስተላልፎበታል።
የጋዜጠኛው ቀጣሪ ድርጅት የሆነው ዎል ስትሬት ጆርናል ፍርዱን "አሳፋሪ ፍርድ" ሲል አጣጥሎታል።
የቀረበበት ክስ ሀሰተኛ መሆኑን የሚገልጸው የ32 አመቱ ገርሽኮቪች ባለፈው ወር ነበር በየካተርንበርግ ከተማ የክስ ሂደቱን መከታተል የጀመረው።
ገርሽኮቪች ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በስለላ ወንጀል ተከሶ ሩሲያ ውስጥ ጥፋተኛ የተባለ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሆኗል። የፍርድ ሂደቱን የሚያሳየው በፍርድ ቤቱ የተለቀቀው ቪዲዮ፣ ገርሽኮቪች በመስተዋት በታጠረ ኬጅ (ዙሪያውን የታጠረ ቦታ) ውስጥ ሆኖ ውሳኔውን ወይም ፍርዱን አዳምጧል።
ጥያቄ አለህ ወይ ተብሎ የተጠየቀው ጋዜጠኛው "የለኝም" ሲል መልሷል። ዳኛው አንድሬ ምንየቭ ገርሽኮቪች ከተያዘ ጀምሮ ያሳለፋቸው 16 ወራት ከ16ቱ አመታት ላይ ይቀነሳሉ ብለዋል።
ጃኛው የጋዜጠኛው ሞባይል እና የወረቀት ማስታወሻ እንዲወድም አዘዋል። ጋዜጠኛው አቤቱታ ለማሰማት 15 ቀናት አሉት።
ኃይት ሀውስ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት አለመስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ይህ አሳፋሪ እና በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ክስ የተላለፈው ኢቫን ያለአግባብ ታስሮ 478 ቀናትን በእስር ቤት ካሳለፈ፣ ቤተሰቦቹ እንዳይጠይቁት ከተከለከሉ እና የጋዜጠኝነት ስራውን እንዳይሰራ ከተደገ በኋላ ነው" ብሏል ጋዜጣው ባወጣው መግለጫ።
"ኢቫን እንዲለቀቅ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ቤተሰቦቹንም እንረዳለን። ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም፤ አስከሚለቀቅ ድረስ አናርፍም።"
በዛሬው እለት የነበረው ችሎት የክስ ሂደቱ ከተጀመረ ሶስተኛው ነው። ለወትሮው ብዙ ወራትን የሚፈጀው የስለላ ጉዳይ በዝግ ችሎት በፍጥነት መጠናቀቁ፣ አሜሪካ እና ሩሲያ ገርሽኮቪችን ጨምሮ የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ለማድረግ ጫፍ ላይ መድረሳቸው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ክሬሚሊን በዚህ ጉዳይ መልስ አለመስጠቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ አቃቤ ህግ ገርሽኮቪች በአሜሪካ ሴንተርራል ኢንተሊጀንስ ኤጀንስ ትዕዛዝ በስቬርድሎቭስክ ግዛት ስላው የታንክ ማምረቻ ኩባንያዎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ሰብሰቧል ብለዋል። ገርሽኮቪች እና ጋዜጣው ይህን ውድቅ አድርገውታል።
ከሩሲያ የፌጀራል ሴክሪቲ ሰርቪስ ( ኤፍኤስቢ) የመጡ ሰራተኞች ገርሽኮቪችን በፈረንጆቹ መጋቢት 29፣2024 ነበር ከሞስኮ 1400 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የካተርንበርግ ከተማ በቁጥጥር ስር ያዋሉት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሩሲያ ሌቨርቶቮ እስር ቤት ታስሮ ቀይቷል።
ጋዜጠኛው የተከሰሰበት የስልላ ወንጀል በሩሲያ እስከ 20 አመት እስራት ያስቀጣል።
ሩሲያ ብዙ ጊዜ የእስረኛ ልውውጥ ስምምነት ከማድረጓ በፊት የህግ ሂደቶች እንዲጠናቀቁ ታደርጋለች።