ጸረ አውሮፓ ህብረት አቋም ያለው ፓርቲ የኔዘርላንድ ምርጫን አሸነፈ
በአውሮፓ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች የህዝብ ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል
ስፔን፣ ጀርመን፣ ሀንጋሪ እና ፈረንሳይ በስደተኞች ላይ የከረረ አቋም የያዙ ፓርቲዎች ተቀባይነታቸው እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል
ጸረ አውሮፓ ህብረት አቋም ያለው ፓርቲ የኔዘርላንድ ምርጫን አሸነፈ።
በኔዘርልንድ በተካሄደ የህግ አውጪ ምክር ቤት የአውሮፓ ህብረትን የሚቃወም ፓርቲ አብዛኛውን መቀመጫ አሸንፏል።
አውሮፓ ህብረትን የሚጠራጠሩት እና በስደተኛ ፖሊሲ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ የሚፈልገው ግሪት ዌልደርስ በምርጫው ድል ቀንቶታል።
ይህ ቀኝ ዘመም ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር አብዛኛውን የሀገሪቱን ህግ አውጪ ምክር ቤት መቀመጫ ለአውሮፓ ህብረት ራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል ዴይሊ ኤክስፕረስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ይህ ፓርቲ መንግሥት ከመሰረተ በኋላ ኔዘርላንድ የአውሮፓ ህብረትን እንድትለቅ ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂድ እንደሚችልም ተሰግቷል።
ከቅርብ ጊዜያት በኋላ በአውሮፓ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የህዝብ አመኔታን እያገኙ የመጡ ሲሆን ይህም ለህብረቱ መፍረስ በስጋትነት ተለይቷል።
ምርጫ ያሸነፈው ይህ የኔዘርላንድ ቀኝ ዘመም ፓርቲ አውሮፓ ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲ እንዲከተል ከመፈለጉ ባለፈ ከእስልምና እምነት እና ሽብርተኝነት ጋር በተያያዘም ተቃውሞ አለው ተብሏል።
ቀኝ ዘመሟ የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ እና የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክተር ኦርባን ህብረቱ እንዲሻሻል በመወትወት ላይ ናቸው።
በፈረንሳይ፣ በስፔን እና በጀርመን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በህዝብ እየተወደዱ መምጣታቸው በቀጣም የሚካሄዱ ምርጫዎችን በማሸነፍ ወደ መሪነት ሊመጡ እንደሚችሉም ሰፊ ግምት አለ።
ከአንድ ወር በፊት ስሎቬኪያ ባካሄደችው ተመሳሳይ ምርጫ የሩሲያ ወዳጅ መሪ ጠቅላይ ሚንስትር ተደርገው መመረጣቸው ተገልጿል።
ብሪታንያ ከአምስት ዓመት በፊት ባካሄደችው ህዝበ ውሳኔ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መነጠሏ ይታወሳል።