የአውሮፓ ህብረት 223 ቢሊዮን ዶላር የሩሲያን ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ አግዷል
ሩሲያ የአውሮፓ ህብረትን አስጠነቀቀች፡፡
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት 20ኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን ጦርነቱ በርካታ ትዕይንቶች ተስተናግደውበታል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ በርካታ ማዕቀቦችን የጣለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የሩሲያ መንግስት እና ዜጎች ንብረት የሆኑ የባንክ መዝገቦችን እንዳይንቀሳቀሱ አግዷል፡፡
በአጠቃላይ በህብረቱ እገዳ የተጣለበት የሩሲያዊያን ገንዘብ 223 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህ ገንዘብ ሌክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል መወሰኑ ተገልጿል፡፡
የህብረቱ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊን ዩክሬን ለደረሰባት ውድመት ካሳ አልያም ለመልሶ ግንባታ በሩሲያ ወጪ መሸፈን አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ለህብረቱ በሰጠችው ምላሽ የአውሮፓ ህብረት የሩሲያዊያንን ገንዘብ ለዩክሬን ከሰጠ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡
የአውሮፓ ህብረት ሀገራት በሩሲያ ምን ያህል ገንዘብ እንዳላቸው በግልጽ ያልተጠቀሰ ሲሆን ህብረቱ ያሰበውን ህገወጥ ስራ እንዲያቆም ሞስኮ አሳስባለች፡፡
ከ22 ቀናት በፊት በእስራኤል እና ሀማስ መካከል የተፈጠረው ጦርነት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ትኩረታቸውን ከዩክሬን ላይ እንዲያነሱ ማድረጉ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎም ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያደረገች ያለውን የአየር እና የምድር ላይ ጥቃት አስፋፍታለች የተባለ ሲሆን ዩክሬን በበኩሏ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲደረግላት በመጠየቅ ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዩክሬን በቀጣዩ መጋቢት ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይደረጋል መባሉ ዩክሬናዊያንን እና አጋሮቿን የከፋፈለ ሲሆን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በምርጫው ሊሸነፉ ይችላሉ የሚል ስጋትም አለ ተብሏል፡፡