ቤሩትን ለከበደ ፍንዳታ የዳረጋት አሞኒዬም ናይትሬት ምንድነው?
ማዳበሪያዎችን ለመስራት የሚያገለግለው አሞኒዬም ናይትሬት ለረዥም በሁኔታዎች ሊቀጣጠል የሚችል ነው
ፍንዳታው ላለፉት 7 ዓመታት በመጋዘን ተከማችቶ በቆየ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ምክንያት የተፈጠረ ነው ተብሏል
ቤሩትን ለከበደ ፍንዳታ የዳረጋት አሞኒዬም ናይትሬት ምንድነው?
የሊባኖስን ርዕሰ ከተማ ቤሩትን ያንቀረቀበው ፍንዳታ በከተማዋ ወደብ በሚገኝ አንድ መጋዘን ተከማችቶ በቆየ የአሞኒዬም ናይትሬት የምርት መጠን ማሳደጊያ ግብዓት (ማዳበሪያ) ምክንያት ያጋጠመ ነው፡፡
ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዲያብ አረጋግጠዋል፡፡
በመጠን ከ2 ሺ 750 ቶን በላይ ነው የተባለው የምርት መጠን ማሳደጊያ ማዳበሪያው እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ ላለፉት ከ7 በላይ ዓመታት በመጋዘኑ ተከማችቶ ስለመቆየቱም ተነግሯል፡፡
ለመሆኑ ቤሩትን እንዲህ ለከበደ ፍንዳታ የዳረጋት አሞኒዬም ናይትሬት ምንድነው?
አሞኒዬም ናይትሬት በተፈጥሮ የሚገኝ ኬሚካላዊ ውህድ ነው፡፡ NH4NO3 በተሰኘ ኬሚካላዊ ቀመሩም ይታወቃል፡፡ ነጭ መስተዋት መሰል ጠንካራ አካላዊ ቅርጽ ያለውም ሲሆን በቀላሉ በቶሎ በውሃ ሊሟሟ የሚችል ነው፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የኬሚካሉ ክምችት በቺሊ አታካማ በርሃ ይገኛል፡፡
በቀዳሚነት ምርትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሰው ሰራሽ የግብርና ግብዓቶችን (ዩሪያና ዳፕን መሰል ማዳበሪያዎች) ለማምረት ያገለግላል፡፡ በተለይ ከናይትሬት አሲድ ጋር ሲቀላቀል ተፈላጊውን የሰው ሰራሽ ምርት በቀላል ዘዴ ለመስጠት ያስችላል፡፡ ለማምረት ቀላል ሲሆን በዋጋም ውድ የሚባል አይደለም፡፡ ይህም ሌሎች ግብዓቶችን ለማዘጋጀት ከሚያስችሉ የኬሚካል ዓይነቶች ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
በተለያዩ የግንባታ እና የማዕድን ስፍራዎች ግልጋሎት ላይ ለሚውሉ ደማሚትን መሰል ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ለማምረትም ይውላል፡፡ ለዚህ ግልጋሎት ከሚውለውና በምህጻረ ቃሉ ‘ANFO’ ከተሰኘው ፈሳሽ አብዛኛው ይኸው ኬሚካል ነው፡፡
አሞኒዬም ናይትሬት አይተንም፡፡ በራሱ ሊያጋልጥ የሚችል ወይም አደገኛም አይደለም፡፡ ሆኖም የአያያዝ፣የአቀማመጥ ሁኔታዎች አደገኛ እንዲሆን አደጋንም እንዲፈጥር ሊያደርጉት ይችላል፡፡ ይህን ታሳቢ አድርገው ጥብቅ የቁጥጥር መመሪያዎችን አውጥተው ተግባራዊ ያደረጉ ሃገራትም ጥቂት አይደሉም፡፡
አሞኒዬም ናይትሬት በምን ምክንያት ሊፈነዳ ይችላል?
የተረጋጋ ነው በሚል በኬሚስትሪ ሳይንስ ጠበብቶች የሚነገርለትን አሞኒዬም ናይትሬትን አንዳንድ ሁኔታዎች ካለ አንዲት ጠብታ ነዳጅ ሊያፈነዱት ወይም ሊያቀጣጥሉት ይችላሉ፡፡
ኬሚካሉ ለረዥም ጊዜ በተቀመጠ ቁጥር የመብላላትና ሙቀትን የማመንጨት ተፈጥሮ አለው፡፡ ከፍ ያለ መጠን ባለው ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ተከማችቶ የሚቀመጥም ከሆነ በራሱ ሊቀጣጠል ከፍተኛ ፍንዳታንም ሊፈጥር ይችላል፡፡
በሚቀጣጠልበት ጊዜ ደግሞ የሚፈጠሩ ኬሚካላዊ አጸግብሮቶች አሉ፡፡ እነዚህ አጸግብሮቶች ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ኦክስጅን እንዲመረት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ኦክስጂን ደግሞ የሚቀጣጠለው ነገር የበለጠ እንዲያያዝ ለማድረግ የሚያስችል ተፈጥሯዊ አቅም አለው፡፡