በአሜሪካ የጸረ-ሙስሊም ጥቃቶች 180 በመቶ መጨመራቸው ተገለጸ
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር በሙስሊሞች እና በጀዊሾች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የሙስሊም እና ጸረ- ፍልሴጤማውያን ጥላቻ በአሜሪካ እና በሌላው ዓለም እየጨመረ መጥቷል ተብሏል
በአሜሪካ የጸረ-ሙስሊም ጥቃቶች 180 በመቶ መጨመራቸው ተገለጸ።
ሀማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ጥቃት ካደረሰበት ከፈረንጆቹ ጥቅምት 7፣ 2023 ወዲህ ባሉት ሶስት ተከታታይ ወራት ውስጥ በአሜሪካ የጸረ- ሙስሊም እና ጸረ-ፍልሴጤማውያን ማግለል እና ጥላቻ 180 በመቶ መጨመሩን የመብት ተሟጋች ቡድን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
ሮይተርስ ቡድኑን ጠቅሶ እንደዘገበው የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የሙስሊም እና ጸረ- ፍልሴጤማውያን ጥላቻ በአሜሪካ እና በሌላው ዓለም እየጨመረ መጥቷል።
በአሜሪካ በህዳር ወር በሶስት ፍልስጤማውያን ተማሪዎች ላይ የደሰው ግድያ እና በጥቅምት ወር በኢሊኖይስ የፍልስጤም እና የአሜሪካ ዜግነት ባላት የስድስት አመት ህጻን ላይ የደረሰው ጉዳት የጥቃቱን መጨመር የሚያሳዩ ክስተቶች ናቸው ተብሏል።
የአሜሪካ እስላሚክ ሪሌሽንስ ካውንስል (ሲኤአይአር) በትናንትናው እለት እንደገለፈው በ2023 የመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት 3578 ቅሬታዎችን ተቀብሏል።
የጸረ-ሙስሊም እና ጸረ- ፍልስጤማውያን ጥላቻ በሰፊው እየተስተዋሉ መሆኑን የገለጸው ካውንስሉ የቀረበው ቅሬታው ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 178 በመቶ አድጓል ብሏል።
662 የስራ ቦታ ቅሬታዎች ፣ 472 የጥላቻ ወንጀሎች እና አጋጣሚዎች፣ 448 የትምህርት ቦታ መገለል ቅሬታዎችን መቀበሉን ካውንሰሉ ገልጿል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የጸረ-ስም ማጥፋት ሊግ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት ሰባት በኋላ ባሉት ሶስት ተከታታይ ወራት የጸረ-ጽዮናዊ ጥቃቶች ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 360 በመቶውን መጨመሩን ሪፖርት አድርጎ ነበር።
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር በሙስሊሞች እና በጀዊሾች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ፕሬዝደንት ባይደንም ጸረ-ጽዮናዊነትን እና የመስሊም ጥላቻን አውግዘዋል።