ቤጂንግ በወታደሮቼ ላይ የሚፈጸሙ ክብረ ነክ ድርጊቶችን አልታገስም ማለቷ ተሰምቷል
ቻይና በወታደሮቿ ላይ ያሾፈን ግለሰብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ቀጣች።
የዓለማችን ሁለተኛዋ መሪ ሀገር የሆነችው ቻይና በወታደሮቼ ላይ የሚፈጸም ክብረ ነክ ድርጊቶችን አልታገስም ብላለች።
ሊ ሀዎሺ የተሰኘው ቻይናዊ አስቂኝ ስራዎችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን በሀገሪቱ ወታደሮች ላይ የተቀለደ ይዘትን ለተከታዮች አቅርቧል።
በቤጂንግ በተሰናዳ አንድ መድረክ ላይ የቀረበው ይህ ቀልድ የሀገሪቱን መንግሥት እንዳስቆጣ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም በግለሰቡ ላይ የቻይናን ብሄራዊ ወታደሮች ክብር ይነካል፣ ወታደሮቹ ለሀገራቸው እየከፈሉት ባለው መስዋዕትነት ላይ ተሳልቋል በሚል ክስ ቀርቦበታል።
ግለሰቡ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ውሳኔ የተላለፈት ሲሆን ጉዳዩ ቻይናዊያንን ለሁለት መክፈሉ ተገልጿል።
የቤጂንግ ባለስልጣናትም ሺያጉ በተሰኘ ኩባንያ ስር ስራዎቹን እያቀረበ ባለው የአስቂኝ ስራዎች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል ተብሏል።
ኩባንያውም ለተመልካቾች ያቀርብበት የነበረው መድረክ ላይ እገዳ የተላለፈበት ሲሆን የኮሜዲ ስራዎችን ያቀረበውን ግለሰብ ማሰናበቱን አስታውቋል።
በፈረንጆቹ 2021 ላይ ኩባንያው እና ግለሰቡ ያልተገባ ነገር ለህዝብ አቅርባችኋል በሚል ጥፋተኛ ናችሁ በሚል የ26 ሺህ ዩሮ ቅጣት ተላልፎባቸዋል ተብሏል።