ድርድሩ ከተሳካ የአፕል ምርቶችን የሚጠቀሙ ቻይናዊያን ባይዱ ሰራሽ የሆነው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን መጠቀም ይችላሉ ተብሏል
አፕል ኩባንያ ከቻይናው ባይዱ ጋር መደራደር ጀመረ፡፡
የዓለማችን ቀዳሚ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች አምራች የሆነው አፕል ኩባንያ በቻይና ያሉ ደንበኞቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ድርድር በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በአንዳቸው ኩባንያዎች ላይ ማዕቀቦችን መጣላቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ የቻይና ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ እና ሌሎች መረጃዎችን የሰልሉኛል በሚል ማዕቀቦችን ጣለች ሲሆን ቻይናም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ናት፡፡
ለአብነትም አሜሪካ በቻይናው ህዋዌ ኩባንያ ምርቶች ላይ ማዕቀብ ስትጥል ቻይናም በአፕል ምርቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡
እንዲሁም ቻይና የአሜሪካውን ጎግል የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ኩባንያ እንዳይሰራ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ ለዚህ አቻ የሆነ ባይዱ የተሰኘ ተቋም አላት፡፡
መሰረታቸውን አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት ያደረጉ ጎግልን እንደ ዋነኛ የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል አድርገው የሚጠቀሙ ኩባንያዎች ሰፊ የገበያ ድርሻ ባላት ቻይና እንደልባቸው መስራት አልቻሉም፡፡
ለዚህም ሲባል አፕል ኩባንያ በቻይና ያሉ ደንበኞቹ የባይዱ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶችን መጠቀም እንዲችሉ በመደራደር ላይ እንደሆነ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡
ቻይና የአፕል ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እገዳ ጣለች
የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ በቻይና ምርቱን ለሚጠቀሙ ደንበኞቹ ሲል ከቻይናው ባይዱ ጋር የአጋርነት ስምምነት አስቀድሞ ተፈራርሟል ተብሏል፡፡
ቻይና በኦፕን አይ የተሰራው ቻትጅፒቲ የተሰኘው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት በሀገሯ እንዳይሰራ ያገደች ሲሆን የራሷን አቻ ምርት በባይዱ በኩል ይፋ አድርጋለች፡፡
በዚህ ምክንያትም ሰፊ ሸማች ህዝብ ያላት ቻይና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የባይዱን ሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርቶችን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡