ቻይና የአፕል ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እገዳ ጣለች
ቤጂንግ የአሜሪካው አፕል ኩባንያ ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ያገደችው ከደህንነት ጋር በተያያዘ ነው
ቻይና ከአፕል በተጨማሪ በውጭ ሀገራት የተመረቱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችንም በሀገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አግዳለች
ቻይና የአፕል ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እገዳ ጣለች።
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና የአፕል ምርቶችን ላለመጠቀም መወሰኗ ተገልጿል።
ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል ሰፊ ሸማች ባላት ቻይና ታግዷል።
እገዳው የአፕል ኩባንያ ገቢን በእጅጉ ይጎዳል የተባለ ሲሆን ቤጂንግ አይፎንን ጨምሮ የአፕል ምርቶችን ሁሉ ማገዷን አስታውቃለች።
እንደ ዎልስትሪት ዘገባ ከሆነ ቻይና የአፕል ምርቶችን በመንግስት ተቋማት ጥቅም ላይ እንዳይውል እገዳ የጣለችው ከደህንነት ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ሀገሪቱ ከአፕል ኩባንያ ምርቶች በተጨማሪም በውጭ ሀገራት ተመርተው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ሁሉ ጥቅም ላይ እንዳይዉሉ አግዳለች ተብሏል።
አፕል ኩባንያ ከአጠቃላይ ገቢው 19 በመቶውን ከቻይና ደንበኞቹ የሚያገኝ ሲሆን በቻይና በርካታ ቦታዎች ምርቶቹን በማምረት እና በመሸጥ ላይ ይገኛል።
የቤጂንግ አዲስ ውሳኔ አሜሪካ በቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ እያደረገችው ላለው እገዳ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።
አፕልምም ሆነ የቻይና መንግስት ግን ስለእገዳ ውሳኔው እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።
ከሁለት ሳምንት በፊት ሌላኛዋ የእስያ ሀገር ሕንድ በውጭ ሀገራት የተመረቱ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ እገዳ መጣሏ ይታወሳል።
ሕንድ እገዳውን የጣለችው የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን ለመከላከል በሚል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾም ነበር።