ልዩልዩ
የአለማችን ፈጣኑ የአፕል ላፕቶፕ ምን ያህል ዋጋ ተቆረጠለት?
ኩባንያው ከዚህ ቀደሞቹ በስድስት እጥፍ ፈጣን የሆኑ ማክቡክ ፕሮ ኮምፒውተሮችን ነው ለገበያ ያቀረበው
ፈጣን ኮምፒውተሮቹ በ1 ሺህ 999 እና 2 ሺ 499 ዶላር ለገበያ ቀርበዋል
የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ አፕል በአለማችን ፈጣኑን ላፕቶፕ ኮምፒውተር ለገበያ ማቅረቡ ተሰምቷል።
ኩባንያው እጅግ ፈጣን ናቸው የተባሉ ኤም2 ቺፕ የሚጠቀሙ ማክቡክ ፕሮ ኮምፒውተሮችን ነው ለገበያ ያቀረበው።
አፕል ከዚህ ቀደም የሚጠቀማቸውን የኢንቴል ቺፖች በራሱ አቅም ባመረታቸው ኤም2 ፕሮ እና ሜም2 ማክስ ቺፖች መተካቱን አስታውቋል።
ይህም የማክቡክ ፕሮ ኮምፒውተሮቹን ፍጥነት ከዚህ ቀደሞቹ በስድስት እጥፍ ፈጣን እንዲሆኑ ማድረጉን ነው ዴይሊ ሜል ያስነበበው።
ኤም2 ፕሮ ቺፕስ የተገጠመለት ማክቡክ ፕሮ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ከማክቡክ ኮምፒውተር 40 ከመቶ በላይ ፈጣን ነው ብሏል አፕል።
ኮር አይ9 ከሆነው ማክቡክ ደግሞ 80 በመቶ ብልጫ ያለው ፍጥነትን አሳይቷል ነው የተባለው።
16 ጊጋባይት ራም እና 512 ጊጋባይት ያለው ማክቡክ ፕሮ፥ በ14 እና 16 ኢንች አማራጮች ነው የቀረበው።
ባለ14 ኢንቹ በ1 ሺህ 999 የአሜሪካ ዶላር፤ ባለ16 ኢንቹ ደግሞ በ2 ሺህ 499 ዶላር ለገበያ መቅረባቸውም ተገልጿል።
አፕል በ599 የአሜሪካ ዶላርም ተመሳሳይ ፍጥነት ያለው ማክ ሚኒ ለሽያጭ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል።