ሳምሰንግ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን የሚጠቀምና በስልክ ጥሪ ወቅት ቀጥታ ቋንቋዎችን የሚተረጉም ስልኩን ይፋ አደረገ
ጋላክሲ S24 የመጀመሪው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተገጠመለት ስልክ ሆናል
አፕል ኩባንያም በቅርቡ ተመሳሳይ ምርት እንደሚያመርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል
ሳምሰንግ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በስፋት መጠቀም የሚያስችሉ ጋላክሲ S24 ስማርት ስልኩን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ ስልክ አፕል እና ህዋዌ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያዎችን ለመፎካከር የሚያስችለውን አዲስ ስሪት ስማርት ስልኩን ከሰሞኑ አስተዋውቋል።
ኩባንያው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚስችለው የመጀመሪያ ምርቱ ጋላክሲ S24 በሚል ወደ ገበያ ይዞ እንደሚወጣ አስታውቋል።
የሳምሰንግ ሞባይል ክፍል ፕሬዝዳንት ቲኤም ሮህ እንዳሉት ደንበኞቻችን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን የበለጠ በፈለጉት ቦታ እና ጊዜ መጠቀም የሚያስችላቸውን የስልክ ቀፎዎች ይፋ አድርገናል ብለዋል።
ሳምሰንግ ጋላክሲ S24 ስልክ በ1 ሺህ 300 ዶላር ለገበያ ይቀርባል የተባለ ሲሆን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮም ለሸማቾች እንደሚቀርብ ተገልጿል።
አዲሱ የስልክ ቀፎ በተለይም ሀሰተኛ ምስሎችን እና ሌሎች መረጃዎችን በቀላሉ መለየት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ተገጥሞላቸዋልም ተብሏል።
ይህ ስልክ በተገጠሙለት ሶፍትዌሮች አማካኝነት የዕለት ሪፖርቶችን ገምግሞ ያቀርባል የተባለ ሲሆን ፈቃደኝነትን መሰረት በማድረግ ስልኩ በራሱ ብዙ አይነት አገልግሎቶችን እና ሪፖርቶች ይሰጣልም ተብሏል።
በተጨማሪም ስማርት ስልኩ በማናውቀው ቋንቋ ሰዎች ከደወሉልን በንግግሩ ወቅት በቀጥታ ይተረጉምልናል የተባለ ሲሆን፤ አሁን ላይ 13 ቋንቋዎችን እንደሚተረጉምም ነው ኩባያው ያስታወቀው።
እንዲሁም ቪዲዮ ኤዲት የሚያደርግ መተግበሪያም ያለው ስማርት ስልኩ፤ ፍጥነት ያላቸው ቪዲዮዎችን ወደ ዝግታ (ስሎው ሞሽን) መቀየርም ያስችለናል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ከኮምፒውተሮች ውጪ ባሉ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ እንዳይሰራ በሚል የነበረው የባለሙያዎች ክርክር ሳይሳካ ቀርቶ አገልግሎቱ ወደ እጅ ስልኮችም በመዛወር ላይ ይገኛል።
የአፕል ኩባንያ ምርት የሆነው አይፎንም ተመሳሳይ ስልኮችን እንደሚያመርት ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ ይፋ ያደረገ ቢሆንም ሳምሰንግ ከሁሉም የዓለማችን ኩባንያዎች ቀድሞ ምርቱን ለገበያ አቅርቧል።
ሳምሰንግ አሁን ላይ የእጅ ስልክ ቀፎዎችን በብዛት የሸጠ ቁጥር አንድ የዓለማችን ኩባንያ መሆን የቻለ ሲሆን አፕል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የደቡብ ኮሪያው የኤሌክትሪኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ በሳተላይት የሚሰሩ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮችን አመርታለሁ ማለቱ ይታወሳል።