ሞስኮ አንድ ሽህ የአፕል ሞባይል መሳሪያዎች በአሜሪካ የደህንነት ተቋም ተበክለዋል ብላለች
ሩሲያ "አፕል" ስልኮችን ተጠቅሞ ለአሜሪካ አሰልሎኛል ስትል ከሰሰች።
የሩሲያ ደህንነት አፕል ከአሜሪካ የስለላ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር "አይፎን ስልኮችን" ለመጥለፍ ስውር የስለላ መረብን ተጠቅሟል ሲል ከሷል።
የሩሲያ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌርን በመጠቀም በሽህዎች የሚቆጠሩ አይፎን ስልኮችን ያበላሸውን የአሜሪካ የስለላ ሴራ ማግኘቱን አስታውቋል።
ኤፍኤስቢ በሰጠው መግለጫ የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት የአፕል ሞባይል መሳሪያዎችን በመጠቀም የስለላ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።
ሴራው በአፕል እና በአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ መካከል 'የቅርብ ትብብር' አሳይቷል ብሏል።
ኤፍኤስቢ አፕል የስለላ ዘመቻው ላይ ስለመተባበሩ ወይም ግንዛቤ እንደነበረው የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረበም።
አፕል በሰጠው መግለጫ ክሱን አጥብቆ ውድቅ አድርጓል ሲል ደይሊ ሜል ዘግቧል።
ኩባንያው ከየትኛውም መንግስት ጋር በጭራሽ ተባብሬ ሰልየ አላውቅም ብሏል።
ኤፍኤስቢ እንደገለጸው በሀገር ውስጥ የሩሲያ ተጠቃሚዎች እንዲሁም በሩሲያ እና በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የሚገኙ የውጭ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአፕል መሳሪያዎች ተበክለዋል።