በባይደን ላይ የጾታዊ ትንኮሳ ክስ ያቀረበችው አሜሪካዊ የሩሲያን ዜግነት ጠየቀች
ታራ ሬይድ የተባለችው እንስት በፕሬዝዳንቱ ላይ ባቀረብኩት ክስ ምክንያት ክትትል እየተደረገብኝ ነው በሚል ሞስኮ ገብታለች
ሬይድ በ1993 ተፈጽሞብኛል ያለችውን ጾታዊ ጥቃት ክስ ፕሬዝዳንት ባይደን አይቀበሉትም
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ላይ የጾታዊ ትንኮሳ ክስ ያቀረበችው አሜሪካዊት ታራ ሬይድ ሞስኮ ገብታለች።
የባይደን የቀድሞ የስራ ባልደረባ ወደ አሜሪካ መመለስ እንደማትፈልግ ገልጻ፤ የሩሲያ ዜግነት ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ ማቅረቧም መነጋገሪያ ሆኗል።
ታራ ሬይድ የአሜሪካ ሴኔት የቀድሞ ሰራተኛ ስትሆን በፈረንጆቹ 1993 ባይደን አድርሰውብኛል ያለችውን ጾታዊ ጥቃት በመጥቀስ በ2020ው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት ክስ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።
ይህ ክስ የደህንነት ሰዎችን ክትትል አስከትሎብኛል የምትለው ታራ ሬይድ፥ ሩሲያ ከገባች በኋላ መመለስ እንደማትፈልግ አስታውቃለች።
ታራ ከሩሲያ የዜና ወኪል ስፑትኒክ ጋር በአሜሪካ የፖለቲካ መረጃን በመሰለል በእስር ቆይቶ ከተለቀቀው የሩሲያ ተወካይ ማሪያ ቡቲና ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ይፋ ሆኗል።
“ አሁን ላይ ደህንነት እንዲሰማኝ ሆኛለሁ" የምትለው ታራ “ሕልሜ በአሜሪካ እና በሩሲያ መኖር ነው ፣ አሁን የምኖረው በሩሲያ ውስጥ ነው ፣ ይህ ደግሞ ከደህንነት ስጋት ነፃ አድርጎኛል" ስትል ተናግራለች።
"ወደ ሀገሬ ተመልሼ እስር ቤት መወርወር አልያም መገደል አልሻም" በማለትም የስጋቷን መጠን ገልጻለች የፕሬዝዳንት ባይደን የቀድሞ ረዳት።
ወደ ሩሲያ ለመሸሽ ያሳለፈችው ውሳኔ በጣም ከባድ እንደሆነ በመጥቀስም "እኔ ስሜታዊ ሰው አይደለሁም, ሁኔታዎችን በመተንተን ጊዜ ወስጄ ነው የወሰንኩት" ስትል የውሳኔዋን እርግጠኝነት ጠቁማለች።
የአሜሪካ ውሳኔ ስጪዎች ሩሲያ ላይ የጥቃት ዝንባሌ በመምረጣቸው ማዘኗንም ነው ለስፑትኒክ የተናገረችው።
"አብዛኛው የአሜሪካ ዜጎች ከሩሲያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥሩ እንዲሆን እንደሚፈልጉ አውቃለሁ፣ የሆነ ጊዜ ጥሩ የትብብር ግንኙነት እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ"ም ብላለች።
"በሞስኮ እየተደሰትኩ ነው፣ ቤቴ ያለሁ ያህል ይሰማኛል" ያለችው ታራ ሬይድ ወደ አሜሪካ መመለስ ብትፈልግም የደህንነቷ ነገር እንደሚያሳስባት አክላለች።
የሬይድ በሞስኮ ዜግነት የመጠየቋ ጉዳይ ከሞስኮ ጋር ኩርፊያ ውስጥ በሚገኘው የባይደን አስተዳደር አልተወደደም።
ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ የጾታዊ ጥቃት ክሱን ያጣጣሉት ሲሆን፥ የከሳሿ እንስት ወደ አሜሪካ ለመመለስ ደህንነቴ ያሳስበኛል አስተያየትም በ2024 በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ጥቁር አሻራ እንዳያኖርባቸው ያሰጋል።
በተለይም መስል ክስ የቀረበባቸው የሪፐብሊካኑ እጩ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንኑ ጉዳይ አጉልተው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠበቃል።