ጀርመን በሀገሯ ያሉ አራት የሩሲያን ዲፕሎማሲ ማዕከላትን ዘጋች
ሩሲያ በጀርመን ካላት አምስት የዲፕሎማሲ ማዕከላት ውስጥ አራቱን እንድትዘጋ መደረጉን ኮንናለች
ሩሲያ በሀገሯ ያሉ ጀርመናዊያን ከሰኔ ወር ጀምሮ ለማባረር መወሰኗ ይታወሳል
ጀርመን በሀገሯ ያሉ አራት የሩሲያን ዲፕሎማሲ ማዕከላትን ዘጋች።
ሩሲያ ለጥቂት ቀናት የሚቆይ ልዩ ዘመቻ በሚል ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ ነበር በአውሮፓ ጦርነት የተጀመረው።
ይህ ጦርነት አሁን ላይ 16ኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅዝቃዜ ምክንያት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው ጦርነት አሁን ተፋፍሞ ቀጥሏል።
ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም እና ወታደሮቿን ከዩክሬን እንድታስወጣ በሚል በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል።
ከተጣሉ ማዕቀቦች መካከልም ሞስኮን ከዓለም ዲፕሎማሲ መነጠል ዋነኛው ሲሆን በርካታ የሩሲያ ዲፕሎማቶች ከተለያዩ ሀገራት እንዲሰናበቱ ተደርጓል።
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን በሀገሯ ያሉ የሩሲያ ዲፕሎማሲ ማዕከላት እንዲዘጉ መወሰኗን ተገልጿል።
እንደ ዶቸቪሌ ዘገባ ከሆነ ሩሲያ በጀርመን ካሏት አምስት የኮንስል ጽህፈት ቤቶች መካከል አራቱ እንዲዘጉ ተወስኗል።
በጀርመን መንግሥት እንዲዘጉ ከተወሰኑት የሩሲያ ኮንሱል ጽህፈት ቤቶች መካከልም በሙኒክ፣ ሀምቡርግ፣ ላይፕዝሽ፣ እና ፍራንክፈርት ያሉት ይዘጋሉ ተብሏል።
በርሊን ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ሩሲያ በሀገሯ ያሉ ጀርመናዊያን ከሰኔ ወር ጀምሮ ለማባረር መወሰኗን ተከትሎ ነው።
ሩሲያ በተለያዩ የስራ መስክ በሀገሯ ያሉ ጀርመናዊያንን ከማባረር በተጨማሪ በሞስኮ እና ሌሎች ከተሞች ያሉ የበርሊን ዲፕሎማቶችን እና ሰራተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል።
ሩሲያ በበኩሏ የጀርመንን ውሳኔ ተችታ ጉዳዩ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት እንደሚጎዳ ገልጻለች።