የአፕል ኩባንያ የሰዎችን ሚስጥር በድብቅ በመስማት በቀረበበት ክስ 95 ሚሊየን ዶላር እንዲከፍል ተወሰነበት
ኩባንያው በአይፎን ስልኮች ላይ በሚገኝው “ሲሪ” በተሰኘው የድምጽ አጋዥ አማካኝነት የሰዎችን ንግግር እና የድምጽ ቅጂ ያለፍቀድ ይሰበስብ ነበር ተብሏል
ተቋሙ መሰል ከግል መረጃ አያያዝ እና ሚስጥራዊነት ጋር በተገናኘ በ2024 ብቻ በ3 የተለያዩ ክሶች አንድ ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የካሳ ክፍያ እንዲከፍል ተወስኖበታል
የአፕል ኩባንያ በአንዳንድ የአይፎን ስልኮቹ አማካኝነት የሰዎችን ድምጽ ያለፍቃድ ይሰማ ነበር በሚል በቀረበበት ክስ የተፈረደበትን 95 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል፡፡
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ “ሲሪ” በተሰኝው የድምጽ አጋዥ ቴክኖሎጂው በኩል የደንበኞቹን ሚስጥር በማዳመጥ ክስ ቀርቦበታል፡፡
በተጨማሪም የደንበኞች የድምጽ ቅጂን በሚስጥር በመወስድ ለማስታወቂያ ድርጅቶች ሲሸጥ እንደነበር በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡
የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ ክዶ የተከራከረው ኩባንያ “ሲሪ” የተባለው የድምጽ አጋዥ ቴክኖሎጂ ሰዎች በፍቃዳቸው አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስጀምሩት መሆኑን እንዲሁም በደንበኛው እና በቴክኖሎጂው መካከል የሚደረገው ንግግር በዘላቂነት እንደማይቀመጥ አስተባብሏል፡፡
የድርጅቱ ጠበቆች ከጥቅምት 2019 በፊት በአፕል የተሰበሰቡ የሲሪ የድምጽ ቅጂዎች በቋሚነት መሰረዛቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ እንደሚችሉ ተከራክረዋል፡፡
ከሳሾቹ በበኩላቸው ደንበኞች በተለያየ መንገድ የሚያደርጉትን የስልክ ልውውጥ “ሲሪ”ን በመጠቀም የተቀዱ ድምጾችን ለማስታወቂያ ድርጅቶች በመሸጥ የማስታወቂያ ኢላማ አድርጎናል ብለዋል፡፡
ክሱን ያቀረቡት አካላት ከ2014-2019 ድረስ የአይፎን ስልክ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎችን ወክለው የቀረቡ ቡድኖች ሲሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲከፈል የወሰነውን የ95 ሚሊየን የካሳ ክፍያ እኩል የሚከፋፈሉ ይሆናል፡፡
የአፕል ኩባንያ መሰል ከደንበኞች የግል ሚስጥር እና መረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘ የካሳ ክፍያ ክስ ሲቀርብበት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡
በጃንዋሪ 2024 በአሜሪካ ውስጥ ሆን ብሎ የአይፎን ስልኮች አገልግሎት እንዲዘገይ አድርጓል በሚል በቀረበበት ክስ የ500 ሚሊዮን ዶላር ካሳ በመክፈል ላይ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል በመጋቢት ወር በብሪታንያ ከግል መረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘ በቀረበበት ክስ 490 ሚሊየን ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርበው የአሜሪካው ኩባንያ በ2024 የመጨረሻ 3 ወራት ያገኝው ትርፍ 94.9 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡