አዲስ አመትን እንዲያከብሩ እስረኞችን ፈቶ የለቀቀው የዛምቢያ ፖሊስ
ፖሊሱ በስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ የአዲስ አመት ዋዜምን እንዲያከብሩ 13 ታሳሪዎችን ከፖሊስ ጣቢያ ለቋቸዋል
የሀገሪቱ ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪዎቹን ለማግኝት በፍለጋ ላይ ሲሆን ድርጊቱን የፈጸመው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሏል
በስካር መንፈስ ውስጥ እያለ አዲስ አመትን እንዲያከብሩ 13 እስረኞችን ፈቶ የለቀቀው የዛምቢያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
መርማሪ ኢንስፔክተር ቲተስ ፊሪ የተባለው ፖሊስ በቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪዎቹን በዋና ከተማዋ ሉሳካ ከሚገኘው ሊዮናርድ ቼሎ ፖሊስ ጣቢያ ነው ፈቶ የለቀቃቸው፡፡
ለረጅም ሰአታት በጠጣው መጠጥ በአልኮል ተጽዕኖ ውስጥ የነበረው ኢንስፔክተሩ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ከህግ ለማምለጥ ጥረት አድርጓል፡፡
ባልጠበቁት ሁኔታ ከእስር ቤት እንዲወጡ የተፈቀደላቸው ታሳሪዎች በዝርፊያ ፣ ስርቆት እና አካላዊ ጥቃት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙ ነበሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት ሉሳካ የሚገኘው የሊዮናርድ ቼሎ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊስ አባላት ያመለጡትን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል በአደን ላይ ይገኛሉ፡፡
የፖሊስ ቃል አቀባይ ሬ ሀሙንጋ ድርጊቱን የፈጸመው ኢንስፔክተር ቲተስ ፊሪ በአዲስ አመት ዋዜማ ተረኛ የእስረኞች ጠባቂ ከሆነችው የፖሊስ አባል የእስር ቤቶቹን ቁልፍ በሀይል እንደቀማት ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም ኢንስፔክተሩ የወንድ እና ሴት የእስር ቤት ክፍሎችን በመክፈት "ወደ አዲሱ አመት ለመሻገር ነፃ ሆናችኋል" በማለት ከእስር ቤቱ እንዲወጡ እንዳዘዛቸው ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ ያልተጠበቀውን ድርጊት የፈጸመው መርማሪ ኢንስፔክተር ወዲያው ከአከባቢው ለመሸሽ ቢሞክርም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ኢንስፔክተሩ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸመ እስካሁን ቃሉን አልሰጠም፤ ፖሊስ በበኩሉ ከእስረኞቹ መለቀቅ ጀርባ የስካር ስህተት ወይስ ድብቅ አለማ ያለው የተቀነባባረ ደርጊት የሚለውን ለማጣራት በምርመራ ላይ ይገኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡