ትራምፕ ፑቲንን ማስቆም የሚችሉ ቆራጥ መሪ ናቸው - ዘለንስኪ
ዘለንስኪ 34 ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም ትራምፕ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሰው እንደሆኑ ተናግረዋል
ድርድሩ የሚሳካ ቢሆንም ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል በምስራቅ ዩክሬን በግስጋሴ ላይ የሚገኝውን የሩሲያ ጦር ለማስቆም ትኩረት እንደሚያደርጉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ማስቆም የሚችሉ ቆራጥ መሪ ናቸው ሲሉ ተናገሩ፡፡
በምስራቃዊ ዩክሬን የሩሲያ ሃይሎች ግስጋሴን እየተጋፈጡ የሚገኙት ዘለንስኪ ከዩክሬን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በተያዘው ወር ከትራምፕ በዓለ ሲመት በኋላ በቅድሚያ ዋሽንግተንን ከሚጎበኙ መሪዎች መካከል አንዱ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
ዘለንስኪ ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ለ34 ወራት በዘለቀው ጦርነት ውጤት ላይ ወሳኝ እና የክሬምሊን መሪ ቭላድሚር ፑቲንን ለማስቆም ቁርጠኛው ሰው ናቸው ብለዋል፡፡
በቃለ ምልልሱ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬን ጋር መደራደር ሽንፈት እንደሆነ ያስባሉ፤ ይህም በመሆኑ ድርድሩ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን ትራምፕ በፑቲን ላይ አስፈላጊውን ጫና ለመፍጠር ቆራጥ መሪ እንደሆኑ አምናለሁ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የትራምፕ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ውጤታማነት ላይ እምነት እንዳላቸው ቢገልጹም፤ በተለይ በምስራቃዊ ዩክሬን የሩስያን ጦር ግስጋሴ ለመግታት ጦሩን በሰው ሀይል እና በመሳሪያ ማጠናከር ቅድሚያ እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳደር ጦርነቱን ለማስቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ከሩሲያ ጋር በቅርቡ ግንኙነት መፍጠር እንደሚጀምርም ተናግረዋል፡፡
ሞስኮ ለውይይት ክፍት መሆኗን በተደጋጋሚ የተናገሩት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ነገር ግን የትኛውም ድርድር ሩሲያ በጦርነቱ ያስመዘገበችውን ውጤት እና አራት የዩክሬን ክልሎች ወደ ሩስያ መቀላቀላቸውን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል ብለዋል።
ለዩክሬን ፍትሃዊ ሰላም ማስገኘት ማለት ከአጋሮቿ ጠንካራ የፀጥታ ዋስትና ማግኘት ነው ያሉት ዘለንስኪ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ህብረትን እና የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶን መቀላቀል የነዚህ ዋስትናዎች ማረጋገጫ ናቸው ነው ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2019 የተመረጡት ዘለንስኪ ሀገሪቱ በጦርነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እስካለች ድረስ አዲስ ምርጫ ሊካሄድ እንደማይችል ደጋግመው ተናግረዋል፣ ነገር ግን ሁኔታዎች ከፈቀዱ በኋላ እንደገና ለመወዳደር እንደሚያስቡ ገልጸዋል፡፡