የኬንያዋን መንደር ነዋሪዎች እንቅልፍ ያሳጣው ከሰማይ የወረደ ነገር ምንድን ነው?
ክብ ቅርጽ ያለው ቁስ 2 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት እና 500 ኪሎግራም ክብደት አለው ተብሏል

የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ በዝቅተኛ የምድር ምህዋር ውስጥ ከ14 ሺህ ቶን በላይ ቁሶች እንዳሉ ገምቷል
በኬንያ ትንሽ መንደር ከሰሞኑ ከሰማይ ላይ የወረደው ግዙፍ ነገር ነዋሪዎችን አስደንግጧል።
በማኩኒ ካውንቲ ሙኩኩ በተባለችው መንደር የወደቀው ክብ ቁስ 2 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 500 ኪሎግራም ክብደት እንዳለው ተገልጿል።
በመንደሯ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ባያደርስም ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩን የኬንያው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቲቪ ዘግቧል።
ጆሴፍ ሙቱዋ የተባሉት የመንደሯ ነዋሪ "ከብቶቼን ስጠብቅ ከፍተኛ ድምጽ ሰማሁ፤ ግን ምንም ጭስ አላየውም፤ የመኪና አደጋ የደረሰም መሰለኝ፤ ወደ መንገድ ዳር ወጥቼ ብመለከትም የተጋጨ ነገር የለም" ብለዋል።
ሙቱዋ በሁኔታው ተደናግጠው አካባቢያቸውን መቃኘት ሲቀጥሉ በእሳት የተከበበ የመኪና ጎማ የሚመስል ክብ ነገር ከሰማይ በዝግታ ሲወርድ መመልከታቸውንና ዛፎችን ገነዳድሶ ካረፈ በኋላ እሳቱ መጥፋቱንም ያወሳሉ።
"(ቁሱ) ቤት ላይ ወድቆ ቢሆን ኖሮ ከባድ ችግር ይፈጠር ነበር፤ ከዚህ አስደንጋጭ ነገር መውደቅ በኋላ ምን ይከሰት ይሆን በሚል እንቅልፍ አጥተናል" ሲሉም ተናግረዋል።
የኬንያ የስፔስ ኤጀንሲ ባለሙያዎች ወደ ስፍራው በማቅናት የወደቀው ነገር ምንነትን ለማጥናት የሞከሩ ሲሆን ወደ ህዋ የመጠቀ ሮኬት ቁርጥራጭ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።
በሙኩኩ መንደር የወደቀው የቀለበት ቅርጽ ያለው ቁስ ከሮኬት ከተነጠለ በኋላ የሚፈረካከስ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ የየትኛው ሀገር ወይም ኩባንያ ንብረት እንደሆነ የማጣራት ስራው ተጀምሯል።
"እንደዚህ አይነት ቁሶች (በኬንያ የወደቀው ቀለበት) ወደ ምድር ምህዋር ሲመለሱ ራሳቸውን እንዲያቃጥሉ አልያም ወደ ውቅያኖሶች እንዲገቡ ተደርገው የሚሰሩ ናቸው" ብሏል የኬንያ ስፔስ ኤጀንሲ።
ባለፉት ስድስት አስርት አመታት የሀገራት የህዋ ላይ ፉክክር መጠናከር ከሰማይ ላይ የሚወድቁ ቁሶች እንዲበራከቱ ማድረጉን ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ ባለፈው አመት ባወጣው መረጃ በዝቅተኛ የምድር ምህዋር ውስጥ ከ14 ሺህ ቶን በላይ ቁሶች እንዳሉ ገምቷል። ከዚህ ውስጥም ከሲሶ በላዩ ለህዋ ምርምር የማያስፈልጉ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ነው የጠቆመው።
በየአመቱ ከ110 በላይ የሳተላይት ማምጠቅ ሙከራዎች ይደረጋሉ፤ በጥቂቱ 10 ሳተላይቶች እና ሌሎች የምርምር ቁሳቁሶች ወደ ትንንሽ ስብርባሪዎች ይቀየራሉ። ይህም ከህዋ ላይ ወደ መሬት የሚወድቁ ነገሮች እንዲበራከቱ ማድረጉ ነው የተነገረው።
ባለፈው አመት መጋቢት ወር ከአለማቀፉ የስፔስ ጣቢያ የወደቀ ስብርባሪ በፍሎሪዳ የአንድ መኖሪያ ቤትን ጣሪያ በስቶ መግባቱ ይታወሳል።