የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ጉዳይ ለውይይት ሊቀመጥ ነው
ሊጉ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነትን ውድቅ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል
ኢትዮጵያ በበኩሏ የሶማሊያን ሉዓላዊነት አልጣስኩም ማለቷ አይዘነጋም
የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ጉዳይ ለውይይት ሊቀመጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሶስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ይህን ተከትሎም የአረብ ሊግ እና ግብጽን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት የሱማሊያ ሉዓላዊነትን እንደሚያከብሩ ስምምነቱን እንደማይደግፉት ተናግረዋል።
የአረብ ሊግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሊጉ አባል ሀገራት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጉዳይ እንደሚመክር አስታውቋል፡፡
ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብና አውሮፕላን ማረፊያን አሜሪካ እንድትጠቀምበት ፈቀደች
በበይነ መረብ እንደሚካሄድ የተገለጸው ይህ የሚኒስትሮች አስቸኳይ ስብሰባ የፊታችን ረቡዕ እንደሚካሄድ የሊጉ ምክትል ጸሃፊ ሆሳም ዛኪ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የፈረሙት ስምምነት የሚጎዳው ሀገርም ሆነ የሚጥሰው ህግ እንደሌለ ገልጿል።
ይህ የሚኒስትሮች ጉባኤ በሶማሊያ ጠያቂነት እንደተጠራ ሲገለጽ ስብሰባው በሊጉ 12 አባላት ድጋፍ እንዳገኘም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 1991 ጀምሮ ኤርትራ በህዝበ ውሳኔ ሉዓላዊ ሀገር ከሆነችበት ዓመት ጀምሮ ወደብ አልባ ሀገር የሆነች ሲሆን የሕዝብ ፍላጎትን ለመመለስ በሚል አሁን ላይ የባህር በር ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡